የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኢንዱስትሪ ደንበኞች የፍጆታ ሂሳባቸው እንደ ኃይል አጠቃቀማቸው ይለያያል፡፡ ተቋሙ በኢንዱስትሪ ደረጃ ሶስት አይነት የኢንዱስትሪ ደንበኞች ሲኖሩት እነሱም ዝቅተኛ ሀይል ተጠቃሚ፣ መካከለኛ ሀይል ተጠቃሚ እና ከፍተኛ ሀይል ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎች በመባል በሶስት ይከፈላሉ፡፡ የታሪፋቸው መደብ፣ የክፍያቸው አይነትና የሚከፍሉበት ምክንያት ከዚህ በታች እንደሚከተለው በዝርዝር ቀርቧል፡፡nb

1ኛ) የዝቅተኛ ቮልቴጅ ኢንዱስትሪ ታሪፍ 220 ቮልት እና 380 ቮልት

2ኛ) የመካከለኛ ቮልቴጅ ኢንዱስትሪ ታሪፍ 15 ኪሎ ቮልት እና 33 ኪሎ ቮልት

3ኛ) የከፍተኛ ቮልቴጅ ኢንዱስትሪ ታሪፍ ከ66 ኪሎ ቮልት በላይ

ከላይ የተገለጹት የኢንዱስትሪ ደንበኞች ታሪፍ መደብ በቮልቴጅ እና በተመደበዉ ታሪፍ መጠን (tariff rate) ቢለያዩም የሁሉም ኢንዱስትሪዎች የፍጆታ ታሪፍ ክፍያ ዝርዝር እና የሂሳብ ቀመር ተመሳሳይ ነዉ፡፡

በእዚሁ መሰረት የፍጆታ ታሪፍ ዓይነቶችና የሚከፈልባቸዉ ምክንያቶች  እንደሚከተለዉ ይሆናሉ፡፡

1) የኢነርጂ ፍጆታ ክፍያ (Energy Charge)

የኢነርጂ ፍጆታ ክፍያ ኢንዱስትሪዎች በሚጠቀሙበት የኤሌክትሪክ ጉልበት ልኬት መሰረት (ኪሎ ዋት፣ ኪሎ ቮልት አምፒር ወይም የፈረስ ጉልበት ሊሆን ይችላል) አጠቃላይ ማሽነሪዎቹ  አገልግሎት ላይ በዋሉበት ቆይታ ሰዓት (Running Hours) ተባዝቶ በወር የተጠቀሙትን የኤሌትሪክ ኃይል በኪሎ ዋት ሰዓት (ኪ.ዋ.ሰ) ቆጣሪው የሚመዘግበው ሲሆን ይህንኑ በቆጣሪ ማባዣ እና በተመደበዉ ወጥ የታሪፍ መጠን (Flat rate) ብዜት በማስላት የሚገኝ የፍጆታ ሂሳብ  ነዉ፡፡

የኢነርጂ ፍጆታ ክፍያ (በብር) = ወርሀዊ ፍጆታ(በኪ.ዋ.ሰ KWH) X የቆጣሪ ማባዣ(Meter constant)  

X በታሪፍ መጠን 

2) ከፍተኛ ኃይል ፍላጎት ፍጆታ (Demand Charge)

ይህ የፍጆታ ክፍያ አይነት የሚሰላው የኢንዱስትሪ ደንበኞች እየተጠቀሙበት ያለ ጭነት (Sanction Load በኪ.ዋ.፣ በኪ.ቮ.አ፣ በፈ.ጉ)  በአገልግሎት ጊዜ በአገልግሎት ሰጪዉ ኤሌክትሪክ አዉታር (infrastructure) ላይ የሚያሳድረውን ጫና የኤሌክትሪክ  ቆጣሪዉ በየ15 ደቂቃው እየጠበቀ ስለሚለካ ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት መጠን ሲጨምር ስለሚመዘግብ በወር ዉስጥ የተመዘገበዉን ከፍተኛ ኃይል ፍላጎት ንባብ (Recorded Maximum Demand) ከተቀመጠዉ ወጥ ታሪፍ ጋር በማብዛት ተሠልቶ የሚገኝ የፍጆታ ሂሳብ  ነዉ፡፡

የከፍተኛ ኃይል ፍላጎት ፍጆታ (በብር) = በወር የተገኘው ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት መጠን (KW Pmax) x በታሪፍ መጠን

ይህ የከፍተኛ ኃይል ፍላጎት ታሪፍ (Demand Charge Tariff Rate) አዲስ የታሪፍ ማስተካከያ ከመዉጣቱ በፊት የነበረዉን የዝቅተኛ ኃይል ክፍያ ታሪፍ (Minimum Charge Rate) ሙሉ በሙሉ የተካ ነዉ፡፡

3) ፓወር ፋክተር (Power Factor Surcharge)

ይህ የክፍያ ስሌት ኢንዱስትሪዎች በተከሏቸዉ የተለያዩ ማሽነሪዎች ላይ የሚባክነውን ወይም ጥቅም ላይ ያልዋለውን ኃይል  በኪሎ ቮልት አምፒር ሪአክቲቭ ሰዓት (KVARH) ልኬት መጠን  ከፍተኛ  ወይም ዝቅተኛ በመሆኑ ምክኒያት በወር በአማካኝ የተገኘዉን ፓወር ፋክተር ተቋሙ ካስቀመጠዉ የፓወር ፋክተር መጠን (Target Power Factor or Standard Power Factor) ጋር ሲወዳደር ከ0.9 በታች ከሆነ በተቀመጠዉ ፓወር ፋክተር ቀመር መሰረት ከታሪፉ (Tariff Rate) ጋር በማብዛት ተሠልቶ የሚገኝ ክፍያ ነዉ፡፡

ፓወር ፋክተር ሱርቻርጅ (በብር) = (0.9/ አማካይ ፖ.ፋ Pav. -1) ከፍተኛ ፓ.ፋ. Pmax.

 X በታሪፍ መጠን

 4ኛ)  የአገልግሎት ክፍያ (Service Charge)

ይህ የክፍያ አይነት አገልግሎት ሠጪ ካምፓኒዉ ለደንበኞች በሚሠጠዉ አገልግሎት ከቆጣሪ ንባብ እስከ ቢል ህትመት እና ሽያጭ ድረስ ለሚወጣዉ የተለያየ ወጪን የሚሸፍን ሆኖ በአማካኝ ለሁሉም የኢንዱስትሪ ደንበኞች ተመሳሳይ እና ተመጣጣኝ ሆኖ የተቀመጠ የታሪፍ መጠን (Tariff Rate) ነዉ፡፡

ማስታወሻ

ሁሉም የኢንዱስትሪ ታሪፍ ተገልጋይ ደንበኞች ከፓወር ፋክተር ሱርቻርጅ ክፍያ(Power Factor Surcharge) በስተቀር ማሽነሪዎቻቸዉ በስራ ላይ እስከሆኑ ድረስ ሶስቱንም ዓይነት ክፍያዎች በቋሚነት እንዲከፍሉ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሆኖም ግን ደንበኞች የወር አማካኝ የፓወር ፋክተራቸዉ መጠን ከ0.9 በታች ከሆነ ፓወር ፋክተር (Power Factor Surcharge) ክፍያ የሚፈፅሙ ሲሆን  የፓወር ፋክተራቸዉ መጠን 0.9 እና ከዛ በላይ ከሆነ ክፍያ አይጠበቅባቸዉም፡፡