በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ደንበኞች ከሚያወጡት የኤሌክትሪክ ፍጆታ ሂሳብ ከጠቅላላ ወጪያቸው ከግማሽ በላይ የሚሆነው በኃይል ብክነት የሚመጣ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኢነርጂ ባለስልጣን ባደረገው የተለያዩ የኢነርጂ ኦዲት ጥናቶች፤ ከፍተኛ የኃይል ብክነት ደንበኞች በመኖሪያ ቤታቸው በሚጠቀሙባቸው የእንጀራ ምጣድ፣ ምድጃ እና በፋብሪካ ማሽነሪዎች እንደሚከሰት ይጠቁማሉ፡፡

 

ለብክነቱ ዋና ዋና መንስኤዎች የትኩረት ማነስ፣ የኢነርጂ ብቃት ስታንዳርድ እና ህጎች አለመኖር፣ በቤት ውስጥ የምንጠቀምባቸው የኤሌክትሪክ ዕቃዎች የኢነርጂ ብቃታቸው (Efficiency) አነስተኛ መሆን፣ ፋብሪካዎች የሚጠቀሙባቸው ማሸኖች እና ሌሎች ቁሳቁሶች የኢነርጂ ብቃታቸው አነስተኛ እና ያገለገሉ መሆን እንዲሁም ከዚህ በፊት የነበረው ታሪፍ ዝቅተኛ በመሆኑ ደንበኞች የተሻለ የኢነርጂ አጠቃቀምን ባህል እንዳያዳብሩ አድርጓል፡፡

የኃይል ብክነትን ለመቀነስ መደረግ ከሚገባቸው በርካታ መፍትሄዎች መካከል ለጊዜው የማይጠቀሙበትን አምፑል ማጥፋት እንዲሁም ምድጃ፣ ምጣድ፣ ኤሌክትሮኒክስ እና ሌሎች ዕቃዎች አገልግሎት በማይሰጡበት ጊዜ ሶኬታቸውን መንቀል ይጠቀሳል፡፡

በቂ የፀሀይ ብርሀን ሲኖር የኤሌክትሪክ ኃይልን አለመጠቀም፣ ኃይል ቆጣቢ አምፖሎች፣ ምድጃዎችን፣ ምጣዶችንና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን ብቻ መጠቀም፣ የቀድሞ አምፑሎች አለመጠቀም፣ ምድጃ፣ ምጣድ፣ ለረዥም ጊዜ ያገለገሉ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ካሉ በአዳዲስ መቀየርም ሌላው አማራጭ ነው፡፡

በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ጭነት በሚበዛበት ስዓት በተለይ ከጠዋቱ 3፡30 እስከ 6፡00 እና ማታ ከ12፡00 አስከ ምሽቱ 3፡30 ባለው ሰዓት ውስጥ አለመጠቀምም የኃይል ብክነት ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው፡፡

ከመጠን ያለፈ ብርሃን በሚኖርበት ጊዜ የተወሰኑት አምፖሎችን ማጥፋት፣ ትንንሽ የማብሰያ ዕቃዎችን በትልቅ የኤሌክትሪክ ምድጃ አለመጣድ፣ ውሃ ለማሞቅ በፀሀይ ማሞቅያ መጠቀም በተለይ ለሻወር አገልግሎት ከኤሌክትሪክ ማሞቂያ ይልቅ የፀሐይ ብርሃን መጠቀም የተሻለ ነው፡፡

እንዲሁም ከአንድ ፎቅ በላይ የሆነ መኖሪያ ቤት ያላቸው ደንበኞች እና ትልልቅ ሆቴሎች በፀሐይ ኃይል የሚሠራ ውሃ ማሞቂያን ከኤሌክትሪክ ቦይለር ጋር በማቀናጀት መጠቀም፣ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎቻችን የኃይል ብክነት ማሻሻያ እርምጃዎችን በመውሰድና ፓወር ፋክተር ኮሬክተር (PFC) በመግጠም የኃይል ብክነትን መቀነስ ይችላሉ፡፡

ደንበኞች እነዚህንና መሰል የኃይል ብክነትን ሊቀንሱ የሚችሉ መገልገያ መሳሪያዎችን በመጠቀምና የኃይል አጠቃቀም ልማዳቸውን በማስተካከል ሊደረስ የሚችለውን አላስፈላጊ ወጪ መቀነስ ያስችላቸዋል፡፡ በኤሌክትሪክ መስመሩ ላይ የሚፈጥር የኃይል መጨናነቅንም ለመቀነስ አስተዋፆውም ከፍተኛ ነው፡፡