የአገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች የማመንጨት አቅም 4,300 ሜጋ ዋት የደረሰ ቢሆንም የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የማመንጨት አቅም የሚወሰነው ግድቦቻቸው በሚይዙት የውሀ መጠን ነው፡፡

EEu buliding picture

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ከሁሉም የሃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ከ1,400 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል  ማመንጨት አይቻልም፡፡ ይህ የኤሌክትሪክ ሃይል መጠን ከፍላጎቱ ጋር ሲነጻጸር 60% የሚሆነውን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ደንበኛ ብቻ ቢያስተናግድ ነው፡፡ ሁሉም ኃይል ማመንጫ ግድቦች በየደረጃቸው አስተዋጽኦ ቢኖራቸውም ከፍተኛ ሃይል የማመነጨት አቅም ያለው የግልገል ጊቤ 3 የኃይል ማመንጫ ግድብ ነው፡፡

የግልገል ጊቤ 3 የኃይል ማመንጫ ግድብ የማመንጨት አቅም በውሃ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የበልጉ ወቅት ሲዘገይና የውሃው መጠን እየቀነሰ በሄደ ቁጥር ማመንጨት የነበረበትን ያህል  የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት አልቻለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሃይል ማመንጫ ግድቡ አዲስ  በመሆኑ መያዝ የሚችለውን ያህል ውሀ ሙሉ በሙሉ ማጠራቀም አልቻለም፡፡ ይባስ ብሎ ካለፈው አመት ከነበረው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የዘንድሮው የውሀ መጠን ከፍታ በ15 ሜትር ዝቅ ብሏል፡፡ ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት የግድቡ ውሃ ከባህር ጠለል በላይ 834 ሜትር ላይ የነበረ ሲሆን በዚህ አመት ተመሳሳይ ጊዜ 818 ሜትር ላይ ደርሷል፡፡

ለክረምቱ መዳረሻ ከመጋቢት ወር ጀምሮ በአገሪቱ የምስራቅና ደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች ከበልግ ዝናብ ይገኛል ተብሎ የተገመተው የውሀ መጠን በታሰበው ልክ አለመገኘቱና የቀጣዩ ክረምት ዝናብ ወደ ግድቦቹ እስኪገባ ደግሞ ከዚህ በኃላ ቢያንስ ለሰባት ሳምንታት ያህል ጊዜ መጠየቁ የኃይል አቅርቦቱን ጊዚያዊ ችግር እንዲያስተናግድ አስገድዶታል፡፡

በአጭር አገላለፅ በቀጣዮቹ 6 ሳምንታት ለአገሪቱ የሚያስፈልገው የኤሌክትሪክ ኃይል መጠንና በግድቦቹ ያለው የውሀ ከፍታ ሊያስገኝ የሚችለው የኃይል መጠን ሲሰላ ከፍላጎቱ አንጻር በቂ አይደለም፡፡

አሁን ያለው ውሃ ያለ ቁጠባ ጥቅም ላይ ቢውል ደግሞ ክረምቱ ሳይደርስ ማመንጫወቹ ውሀ አልባ ይሆናሉ፡፡ለዚህ ያለው አማራጭ ውሀውን በቁጠባ መጠቀም ብቻ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ በየቀኑ ካለው የኃይል ፍላጎት በአማካይ እስከ ከ700 እስከ 900 ሜጋ ዋት የሚያመነጭ የውሃ መጠንን መቆጠብ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ የውሃ ቁጠባው ቀጥታ በሀይል ስርጭት ቅነሳ ተግባራዊ የሚደረግ ነው፡፡

ግንቦት 9/2011 ዓ.ም በውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የአዲስ አበባ የፈረቃ ፕሮግራም በሶስት ምድብ ተከፍሎ እንደሚከናወን የተገለፀ ቢሆንም በጋዜጣዊ መግለጫው የተነገረው የፈረቃ ፕሮግራም ለደንበኞችም በቂ ጊዜ የማይሰጥ፣ ለአሰራር አመቺ ባለመሆኑ እና የሚቋረጥበት ሰዓት አጭር በመሆኑ ኔትዎርኩ ላይ ጫና በመፍጠር ለተጨማሪ የኃይል መቆራረጥ ምክንያት ስለሚሆን እንደገና ተሻሽሎ በሁለት ፈረቃ እንዲሆን ተወስኗል፡፡

ለደንበኞችም በየዕለቱ በተመሳሳይ ሰዓት ከሚሆን ይልቅ የጠዋትና የምሽት ሰዓታትን መሰረት ባደረገ መልኩ  አንድ ቀን ጠዋት ከጠፋ ሌላ ቀን ከሰዓት ወይም ምሽት ላይ እንዲሆን በማድረግ መርሃ ግብር ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ ተገብቷል፡፡

እንደገና ተሻሽሎ በቀረበው የፈረቃ ፕሮግራም መሰረት በአዲሰ አበባ ከተማ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚቋረጠው ከንጋቱ 11፡00 እስከ ቀኑ 8፡00 እና ከቀኑ 8፡00 እስከ ምሽቱ 4፡00 ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም  ሁሉም የዝቅተኛ መስመር (የቤት ተጠቃሚዎች) ከምሽቱ 4፡00 ጀምሮ እስከ ንጋቱ 11፡00 የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡

በዚህ የኃይል ቅነሳ መርሃ ግብር የድንጋይ ወፍጮዎች እስከ ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓም ሙሉ በሙሉ ሀይል እንዳይጠቀሙ፣ በውጭ ምንዛሪ ግኝት የተሰማሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ሙሉ በሙሉ ሀይል እንዳማይቋረጥባቸው፣ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች 15 ቀን ተጠቅመው በቀጣዩ 15 ቀን እንዳይጠቀሙ፣ በኤክስፖርት መስክ ከተሰማሩ ውጭ ያሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች አንድ ቀን ከተጠቀሙ በኋላ በቀጣዩ አንድ ቀን እንዳይጠቀሙ በቀጥታ መስመር ኃይል የተገናኘላቸው (dedicated line) የጤና፣ የውሃ እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከፈረቃ ውጭ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡

በሌሎች የሃገሪቱ ከልሎች ተግባራዊ የሚደረገው የፈረቃ መርሃ-ግብር በክልል፣ በዲስትሪክትና በአገልግሎት መስጫ ማዕከላት አማካኝነት የሚገለፅ ሲሆን ክቡራን ደንበኞቻችን የፈረቃ መርሃ-ግብሩ እስከ ሰኔ 30 ሊቀጥል የሚችል ስለሆነ የተፈጠረውን ጊዜያዊ ችግር በመረዳት በትዕግስት እንድትጠብቁን እየጠየቅን የፈረቃ መርሃ-ግብሩን ዝርዝር መረጃ በተለያዩ የኮሙኒዩኬሽን አግባቦች የምናሳውቅ ይሆናል፡፡