Print
Hits: 226

eeulogo

ኤሌክትሪክ ለአንድ አገር ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ወሳኝ ከሆኑት የኢነረጂ ዘርፎች መካከል አንዱ ዋነኛው ነዉ፡፡ይህንን ወሳኝ አገልግሎት በሁለም የሃገሪቱ ከተሞችና የገጠር መንደሮች ተደራሽ ማድረግ ደግሞ ወቅቱ  የሚጠይቀው ስራ ነው፡፡

አገራችን ኢትዮጵያም ይህን አገልግሎት ለሁሉም ዜጎቿ ተደራሽ ለማድረግ ከ1998 ዓ.ም ጀምራ የአገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም በመቅረጽ በርካታ ስራዎችን ስታከናውን ቆይታለች፡፡ ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት አዲስ አበባን ጨምሮ 667 ከተሞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማደረግ የተቻለ ሲሆን አሁን በተደረገዉ ከፍተኛ ኤሌክትሪክ የማዳረስ የስራ 7,047 ከተሞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአዋጅ ከተሰጡት ሃላፊነቶች መከከል ፍትሃዊ የሆነ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እውን ማድረግ አንዱ ነው፡፡ ተቋሙ የተጣለበትን ሃገራዊ ሃላፊነት ለማሳካት በብርሃን ለሁሉ ስትራቴጂ መሠረት በ2025 እ.ኤ.አ ከብሄራዊ የሃይል ቋት (ዋናው ግሪድ) 65 በመቶ እና ከብሄራዊ የሃይል ቋት ወጪ (ኦፍ ግሬድ) 35 በመቶ ለሁሉም የሃገሪቱ ዜጎች የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ ለማድረግ ፕሮግራም ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ መርሃ-ግብርም በ2011 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት 130 አዳዲስ የገጠር መንደሮችን/ ከተሞች ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ ማድረግ ችሏል፡፡

ተቋሙ በዕቅድ የያዘውን ፍትሃዊ የኤሌክትሪክ ተደረሽነት እውን ለማድረግ ከብሄራዊ የሃይል ቋት ውጭ የሆነ ኤሌክትሪክ ሃይል በማመንጨት ለህብረተሰቡ ለማዳረስ በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፤

ከብሄራዊ የሃይል ቋት ውጪ የሆነ የኤሌከትሪክ ሃይል (ኦፍ ግሬድ) ማለት ከሃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች ተግባረዊ የሚደረግ፣ አነስተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል ያለው እና ከብሄራዊ የሃይል ቋት ጋር ያልተገናኘ ለአንድ ለተወሰነ አካባቢ ብቻ የሚያገለግል ከሶላር፣ከዲዝል፣ ከውሃ፣ ከንፋስ እና ከጆተርማል የሃይል ምንጮች የሚገኝ የኤሌክትሪክ የኤሌክትሪክ ሃይል ነው፡፡

ተቋሙ ከብሄራዊ የሃይል ቋት ውጪ የሆኑ የ12 ትናንሽ የሙከራ የሃይል ማመንጫ ጣቢያዎች (ኦፍ ግሬድ) ግንባታ ለማከናወን ዓለም ዓቀፍ ጨረታ በማውጣት የኮንትራት ስምምነት ፈጽሟል፡፡

ፕሮጀክቱ ተግባራዊ የሚደረገው በአገሪቱ ስምንት ክልሎች ማለትም በአማራ፣በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በአፋር፣ በደቡብ እና በሶማሌ ክልሎች ነው፡፡

ፕሮጀክቱ በስድስት መደብ (6 Lots) ተከፍሎ በመላ አገራችን በ12 የገጠር ከተሞች ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን በምድብ አንድ ኦሮሚያ፣ በምድብ ሁለት አማራ፣በምድብ ሶስት ደቡብ፣ በምድብ አራት ሶማሊያና ኦሮሚያ፣ በምድብ አምስት አፋርና ትግራይ፣በምድብ ስድስት ጋምቤላ እና ቤንሻንጉል-ጉሙዝ ክልሎች የሚከናወን ይሆናል፡፡

ፕሮግራሙ ሶስት ዋና ዋና ምሰሶዎች ያሉት ሲሆን የመጀመሪው ከብሄራዊ የሃይል ቋት ኤሌክትሪክ ማዳረስ ነው፡፡ ይህም ቀደም ሲል በአገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም የገጠር ከተሞችና መንደሮች ኤሌክትሪክ መረብ (network) የተዘረጋላቸዉ ነገር ግን ቆጣሪ ያልተገናኘላቸዉን ቆጣሪ የማገናኘት ስራን ጨምሮ በአገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም የገጠር ከተሞችና መንደሮች ኤሌክትሪክ መረብ (network) ሲዘረጋ በቅርብ ርቀት ለሚገኙት የገጠር ከተሞችና መንደሮች በ3 ኪ.ሜ ክልል የትራንስፎርመር ተከላ፣ የመካከለኛ፣ የዝቅተኛ መስመሮችን ዝርጋታና ቆጣሪ የማገናኘት ስራ ማከናወነወን ነው፡፡

ሌላው ምሰሶ ደግሞ ከብሄራዊ የሃይል ቋት ውጭ የሆነ የኤሌክትሪክ አቅርቦትን እውን ማድረግ ነው፡፡ ይህም የኤሌክትሪክ መስመር (network) ባልተዳረሰባቸዉ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ማዳረስ ሲሆን ሶስተኛው ምሰሶ ደግሞ ተቋማዊ ለውጥና አቅም ግንባታን ማምጣት ነው፡፡

የፕሮጀክቱ የገንዘብ ምንጭ የአለም ባንክ እና የኢትዮጵያ መንግስት (የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት) ሲሆኑ የፕሮጀክቱ የገንዘብ መጠንም 59,614,998.26 የኢትዮጵያ ብር እና 8,516,758.46 የአሜሪካን ዶላር ነው፡፡

የዲዛይን ጥናትና አስፈላጊ ዶክመንቶችን አሟልተው በአለም አቀፍ ጨረታ ያሸነፉ ሶስት የቻይና አንድ የስፔን ኩባንያዎች ሲሆኑ የፕሮጀክቱን ግንባታ ለማከናወን የኮንትራት ውል ስምምነት ከፈረሙ አራት አለም አቀፍ ኩባንያዎች መካከል ኖራንኮ ኢንተርናሽናል ኮፕሬሽንጉድያን ናንጅንግ እና ሲ.ኢቲ & ኤን.አር የቻይና ኩባንዎች ሲሆኑ ትራማ የተሰኘው ኩባንያ ደግሞ የስፔን ነው፡፡

ፕሮጀክቱ ተግባረዊ ሲደረግ የእዉቀት ሽግግር እና የስራ እድል የሚፈጥር ሲሆን ለ9,637 የመኖሪያ ቤት ደንበኞች፣1,200 ተቋማት የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡

ፕሮጀክቱ የትምህርት፣ የውሃ፣ የጤና፣ የመንግስት፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት፣ የመስኖና የመጠጥ የገቢያ ማዕከላት፣ ሆቴሎች፣ ሱቆች እና ሌሎችም አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ተጠቃሚ የሚያደረግ ሲሆን የፕሮጀክቱ ግንባታ በስድስት ወራት ውስጥ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡