ከሚያዝያ ወር መጨረሻ ጀምሮ በሁለት ፈረቃ ተከፍሎ ይሰጥ የነበረው የኤሌክትሪክ አገልግሎት የፈረቃ መርሃ-ግብር ላይ ማሻሻያ መደረጉ ተገለፀ፡፡

66757829 2613317732013657 5644089568182403072 n

የፈረቃ መርሃ-ግብሩ መሻሻሉ የተገለፀው የውሃ፣ መስኖና ኢነረጂ ሚኒስቴር፣

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል በጋራ በመሆን ሰኔ 01/2011 ዓ.ም በውሃ፣ መስኖና ኢነረጂ ሚኒስቴር መሰብሰቢያ አዳራሽ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡

የፈረቃ መርሃ-ግብሩ የተሻሻለው ለመኖሪያ ቤቶች፣ ኢንዱስትሪዎች እና ለድንጋይ ወፍጮ ተጠቃሚ ደንበኞች ሲሆን የመኖሪያ ቤት ደንበኞች ሙሉ በሙሉ ከኤሌክትሪክ ፈረቃ መርሃ-ግብሩ ውጭ እንዲሆኑ ተደረጓል፡፡

የከፍተኛ፣ የመካከለኛ እና የዝቅተኛ ሃይል ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎች ለሚቀጥሉት አስራ አምስት ቀናት ቀን 50 በመቶ እና ማታ ከምሽቱ አምስት ስዓት እስከ ንጋቱ 11፡00 በሙሉ አቅማቸው እንዲጠቀሙ የተወሰነ ሲሆን የድንጋይ ወፍጮ ተጠቃሚ ደንበኞች ወቅቱ የክረምት  በመሆኑ ብዙም የግንባታ ስራ ስለማይከናወን ለሚቀጥለው አንድ ወር ከዋናው የሃይል ቋት እንዳይጠቀሙ ተወስኗል፡፡

የፈረቃ መርሃ-ግብሩ ተግባራዊ የተደረገው ወደ ግልገል ጊቤ ሶስት፣ መልካ ወካና፣ ቆቃ እና ነሽ  የሃይል ማመንጫ ግድቦች የሚገባው የውሃ መጠን በመቀነሱ ሲሆን  አሁን ወደ ግልገል ጊቤ ሶስት የሃይል ማመንጫ ግድብ የሚገባው የውሃ መጠን እየጨመረ በመምጣቱ የመርሃ-ግብር ማሻሻያ እንዲደረግ አስችሏል ተብሏል፡፡

አሁን ወደ ግልገል ጊቤ ሶስት የሚገባው የውሃ መጠን 830 ሜትር ከፍታ ላይ የደረሰ ሲሆን ግድቡ ባለፈው አመት በዚህ ተመሳሳይ ወቅት 833.47 ሜትር ላይ ነበር፤ በዚህም ግድቡ አምና ከነበረበት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻፀር 3.47ሜ ዝቅ ብሎ ይገኛል፡፡

ግልገል ጊቤ ሶስት የሃይል ማመንጫ ግድብ በሙሉ አቅሙ ማመንጨት ሲችል 1870 ሜዋት/ሰ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት የሚችል ሲሆን ግድቡ በሙሉ አቅሙ ማመንጨት የሚችለው ደግሞ 892 ሜትር ከፍታ ላይ ሲደርስ ነው፡፡

የውሃ፣ መስኖና ኢነረጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ሁሉም የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ ደንበኞች የተሻለ የሃይል አጠቃቅም ባህል በማዳበር የሚደረሰውን የሃይል ብክነት መቀነስ እንደሚገባቸው ገልፀው፤ በ2012 በጀት አመት የሃገሪቱን የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦትን አሁን ካለበት በ8.9% ከፍ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሩ አክለውም የሃይል አቅርቦቱ የሚሻሻለው ከገናሌ ዳዋ 3፣ ከአይሻ የፀሐይ ሃይል ማመንጫ እና ከሌሎች የሃገሪቱ የሃይል ምንጮች ከሚመነጭ የኤሌክትሪክ ሃይል እንደሆነ አስገንዝበው፤ የሃገሪቱን የሃይል ፍለጎት ለማሟላት የግል ሴክተሮችም በጸሐይ፣ በጆተርማል እና በእንፋሎት የሃይል ምንጮች ላይ በመሰማራት በኦፍ ግሪድ ተሰማርተው የኢንንዱስትሪ ፓረርኮች እና የሌሎች ልዩ ትኩረት ለሚሹ ዘርፍች አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን ገልፀዋል፡፡

ሃገሪቱ በ2011 በጀት አመት 13835 ጊጋ ዋት ስዓት ኤሌክትሪክ ሃይል ለማቅረብ አቅዳ የነበረ ሲሆን በ2012 በጀት አመት 16165 ጊጋ ዋት ስዓት ከፍ ለማድረግ አቅዳ በእንቅስቃሴ ላይ ትገኛለች ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ዘላቂነት ያለው የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲኖር ለማድረግ የማሰረጫ መስመሮችን ግንባታ በማሻሻል የአቅም ማሳደግ ስራ መስራት እና ከጎረቤት ሃገራት የሃይል  መስመር በማገናኘት በአገር ውስጥ የሃይል እጥረት ሲያጋጥም በመስመር ከተገናኙ ሃገራት ሃይል መጠቀም ሲቻል ነው ብለዋል፡፡

የማሰራጫ መስመሮችን ግንባታ አቅም ለማሻሻል የ6ቱ፣8ቱ፣14ቱ እና 54ቱ ከተሞች ኔትወርክ ማሻሻያ ፕሮጀክት ተነድፎ ወደ ስራ የተገባ እንደሆነ እና የሃይል እጥረት ሲያጋጥም ከጎረቤት ሃገሮች ሃይል ለመጠቀም የሚያስችል ስምምነት ለማከናወን ከሶስት ሃገሮች ጋር ስራ ተጀምሯል ብለዋል፡፡  

ዋና ስራ አስፈጻሚው አክለውም የሃይል መቆራረጥና መዋዠቅ ችግርን በመቅረፍ ጥራት ያለውና አስተማማኝ የኤኤክትሪክ አገልግሎት ለመስጠት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ አውቶሜሽን  ቴክኖሎጂ ኔትወርክ ማሻሻያ ስካዳ ሲስተም ተግባራዊ እየተደረገ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

የአውቶሜሽን ኔትወርክ ማሻሻያ ስካዳ ሲስተም በስምንቱ ዋና ዋና የሃገሪቱ ከተሞች ተግባራዊ እየተደረገ ሲሆን የስካዳ ሲስተሙ የሚስተዋሉ የሃይል መቆራረጥና መዋዠቅ ችግሮችን ቀድሞ በመረዳት ፈጣንና ቀልጣፋ የጥገና አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ተብሏል፡፡

ተቋሙ በአስቸኳይ ጥገና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የራሱን የጥሪ ማዕከል በማስገንባት በቅርብ ወደ ስራ እንደሚገባ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተገልጸል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት