ኤሌክትሪክ ለአንድ ሃገር ሁለንተናዊ የዕድገት እንቅስቃሴ የማይተካ ሚና ያለው መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡

DSC 79872

ይሁን እንጂ ይህንን መሰረታዊ የሆነውን ዘርፍ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ለማዳረስና ተጠቃሚ ለማድረግ እየተደረገ ባለው ጥረት፤ በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቱ ላይ የሚደረሱ አደጋዎችና ስርቆት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ መጥቷል፡፡

የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት አውታሮች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጓጉዞ ደንበኞች ጋር የሚደርስበትና ደንበኛው የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ የሚረዱ ግብዓቶች ቢሆኑም፤ በሚደርስባቸው ጉዳትና ስርቆት ተቋሙ የተጠቃሚውን የኃይል ፍላጎት ለሟሟላት እያደረገ ያለውን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድረጎታል፡፡

ትራንስፎርመር ደግሞ ከእነዚህ ግብዓቶች አንዱና መሰረታዊ ነው፡፡ ለደንበኞች የኤሌክትሪክ ኃይል ለማሰራጨት ሚናው ከፍተኛ ሲሆን፤ የኃይል ፍላጎት ሲጨምር የትራንስፎርመሩን አቅም ለማሳደግ ካልሆነ በስተቀር መነካካት፣ ለማንሳት ወይም ለማንቀሳቀስ መሞከር እጅግ አደገኛ ከመሆኑ በላይ ለንብረትና ህይወት መጥፋት መንስኤ ይሆናል፡፡

ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህንን ችላ በማለት የስርጭት ትራንስፎርመር ስርቆት በስፋት እየተከናወነ መጥቷል፡፡ በዚህም በተቋሙ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እያደረሰና የአብዛኛው ደንበኞች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚነት እያስተጓጎለ ይገኛል፡፡

ለዚህ ማሳያ ሰሞኑን በአንዳንድ የአዲስ አበባ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳትና ስርቆት መጥቀስ ይቻላል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ስር በሚገኙት አራት ዲስትሪክቶች መካከል በደቡብ አዲስ አበባ ዲስትሪክት ሁለት ትራንስፎርመሮች እንዲሁም በምስራቅ አዲስ አበባ ዲስትሪክት 3 ትራንስፎርመርመሮች እና ሌሎችም በርካታ ንብረትነታቸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሆኑ እና ለሰፊው የህብረተሰብ ክፍል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ ንብረቶችን ኃላፊነት በጎደላቸው እና የራሳቸውን ኪስ ከመሙላት ባለፈ ለሃገራቸው በማያስቡ ጥቂት ግለሰቦች ተዘርፈዋል፡፡

ዝርፈያው የተፈፀመው ጨለማን ተገን በማድረግና በመስመሩ ላይ ኃይል በማይኖርበት ወቅት በመጠቀም ነው፡፡ ይህ በተቋምና ህዝብ ንብረት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ የሚያደርስ ህገወጥ ተግባር ሲሆን፤ ህብተረሰቡ የኤሌክትሪክ ኃይል በአግባቡ እንዳያገኝም የሚያደረግ ነው፡፡

በመሆኑም ህብረተሰቡ ይህንን አውቆ በአካባቢው የሚገኙ የተቋሙ ብሎም የሃገር ንብረቶች የሆኑቱን የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት አውታሮች እንደራሱ ንብረት ሁልጊዜ በንቃት እንዲጠብቅ ተቋሙ ይጠይቃል፡፡

ጥገና የሚያከናውኑ የተቋሙ ባለሞያዎች በመምሰል ንብረቱን የሚነካኩ፣ የሚበጥሱ፣ የሚቀይሩ እና ሌሎች ህገወጥ ተግባሮችን የሚፈፅሙ ግለሰቦች ሲመለከት ህብረተሰቡ ሊከላከላቸው ይገባል፡፡

የተቋሙ ሠራተኞች ቢሆኑም እንኳን ህጋዊ መታወቂያ መያዛቸውን፣ ባጅ ማድረጋቸውንና የደንብ ልብስ መልበሳቸውን ማረጋገጥ፣ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግም ያስፈልጋል፡፡ እንዲሁም የሚያጠራጥር ሁኔታ ካለ በተቋሙ 905 ነፃ የጥሪ ማዕከል በማሳወቅ፣ በአካባቢው በሚገኝ የተቋሙ የአገልግሎት መስጫ ማዕከል በመጠቆምና ከሚመለከተው የህግ አካላት ጋር በጋር በመተበባር ማስቆም እንደሚገባ ተቋሙ ያሳስባል፡፡

የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚገዙና የህዝብ ሃብት የፈሰሰባቸው በመሆናቸው፣ ሁሉም ህብረተሰብ እንደራሱ ንብረት ሊጠብቃቸው ይገባል፡፡