ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና ተደራሽነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና ተደራሽነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ  

ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና ተደራሽነትን ለማሳደግ እየተሰራ እንደሆነ ትናንት ጥቅምት 5 ቀን 2012 ዓ.ም ሜክሲኮ በሚገኝው የተቋሙ መሰብሰቢያ አዳራሽ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡press

ጋዜጣዊ መግለጫው የተሰጠው በተቋሙ የ2011 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም እና በ2012 በጀት አመት የትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ ሲሆን፣ በባለፈው በበጀት አመት በዋናነት የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ማሻሻል፣ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ማስፋት፣ የአገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል፣ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ደንበኞች ቁጥር መጨመር፣ የተቋሙ ገቢ አሰባሰብ እና የፋይናንስ አጠቃቀም ማሻሻል እንዲሁም የኃይል ብክነትን መቀነስ ላይ ትኩረት ተደርጐ እንደተከናወነ የተገልጸው፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ በጋዜጣዊ መግለጫው እንደገለጹት ተቋሙ በ2011 በጀት ዓመቱ ቴክኒካልና ቴክኒካል ያልሆነ የኃይል ብክነት ለመቀነስ    140,682 ቆጣሪዎች ምርመራ ተካሄዶ 311,951.70 ሜጋ ዋት ሀወር ኢነርጂ እና 263.20 በሚሊዮን ብር ከብክነት ማዳን መቻሉን ተናግረዋል፡፡

አቶ መላኩ አክለውም በዓለም ባንክ ፋይናንስ የሚሰራው የስምንቱ ከተሞች ዲስትሪቢዩሽን መልሶ ግንባታና አቅም ማሳደግ ፕሮጀክት ስራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ 195,264 ደንበኞች የኤሌክትሪክ ኃይል ማገናኘት መቻሉን እና የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ተደራሽነት ለማሳደግ በተሰራው ስራ 229 የገጠር ቀበሌዎችና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኝት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

ተቋሙ ከኢነርጂ ሽያጭ 7.256 ቢሊየን ብር በመሰብሰብ 87.66 በመቶ አፈጻጸም ያሳየ ሲሆን ለረዥም ጊዜ ሳይሰበሰብ ከቆየ ውዝፍ ሂሳብ 799.30 ሚሊዮን ብር፣ ከማያገለግሉ ንብረቶች ሽያጭ  43,204,729  በአጠቃላይ 10.123 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ለተቋሙ የሚደርሰው 40 ከመቶ ብቻ ሲሆን ቀሪውን 60 ፐርሰንት ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያስተላልፋል፡፡

 የግብዓት ማነስ፣ የፋይናንስ እጥረት፣ የትራንስፎርመሮች መቃጠልና መዘረፍ፣ የኔትወርክ ችግርና የመሳሰሉት ተግዳሮቶች በበጀት አመቱ ያጋጠሙ ችግሮች መሆናቸውን በጋዜጣዊ መግለጫው  ተገልጿል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል፣ የተቋሙ ገቢ ለመሳደገ፣ የሃይል ብክነትን ለመቀነስ እና አዲስ ደንበኞችን ቁጥር ለመጨመር የሚያስችሉ ስራዎችን በመስራት አንድ ሚሊዮን አዳዲስ ደንበኞችን ኤሌክትሪክ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራም ተገልፀጿል፡፡


Print