ተቋሙ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻልና የደንበኞችን እርካታ ለማሳደግ በርካታ ስራዎች ማከናወኑን ገለፀ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻልና የደንበኞችን እርካታ ለማሳደግ በ2011 በጀት ዓመት በርካታ ስራዎች ማከናወኑን ገልጿል፡፡70416747 2735389156473180 6973441998527135744 n

ተቋሙ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ካከናወናቸው በርካታ ስራዎች መካከል የተቋሙን አደረጃጀት ማሻሻልና የሠው ኃይል ፍላጐትን ማሟላት፣ ተቋሙን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማዘመን፣ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ተደራሽነትን ማሳደግ፣ አስተማማኛ የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ማሳደግ፣ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ደንበኞች ቁጥር ማሳደግ፣ የተቋሙን ገቢ አሰባሰብና የፋይናንስ አጠቃቀም ማሻሻል፣ የአሰራርና ኦዲት ክፍተቶችን መቀነስ እና የኃይል ብክነትን መቀነስ ናቸው፡፡

ከአደረጃጀት አኳያ ተቋሙ ያልተማከለ ስረዓት የዘረጋ ሲሆን፤ በአሁን ወቅት በዘጠኝ ክልሎች፣ በሁለት ከተማ አስተዳደሮች፣ በ28 ዲስትሪክቶች እና በ564 የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት ተደራጅቶ ወደ ስራ ገብቷል፡፡

የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋና ጥራት ያለው ለማድረግ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፉ አሰራር ስርዓት ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ ከእነዚህም መካከል የኢንተርፕራይዝ ሪሶርሰ ፕላኒንግ ሲስተም፣ የአለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርቲንግ ስታንዳርድና ቋሚ ንብረት ምዝገባ እና ዋጋ ትመና ፕሮጀክቶች ይጠቀሳሉ፡፡

የኢንተርፕራይዝ ሪሶርስ ፕላኒንግ የተቋሙን የውስጥ አሰራሮችና ከማዘመን በተጨማሪ የሬዲዮ ኮሚዩኒኬሽን ሲስተም ለመጠቀም፣ የነጻ ጥሪ ማዕከል ለመተግበርና የውስጥ ኢንተርኔት አግልግሎት ለመጠቀም አስችሏል፡፡

ተቋሙ የፋይናንስ አጠቃቀሙን ለማሻሻል አለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርቲንግ ስታንዳርድ እና ቋሚ ንብረት ምዝገባ እና ዋጋ ትመና ፕሮጀክትን በመተግበር ላይ ነው፡፡ የቋሚ ንብረት ምዝገባ እና ዋጋ ትመና ፕሮጀክት በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን፤ በምዕራፍ አንድ የተቋሙ የቤት ውስጥ ንብረት ቆጠራና በምዕራፍ ሁለት ከቤት ውጭ ያሉት ንብረቶች መረጃ የመሰብሰብ ስራ ተሰርቷል፡፡

በበጀት ዓመቱ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ከማሳደግ አንጻር 382 አዳዲስ የገጠር ቀበሌዎችና መንደሮችን፣ በመልሶ ግንባታ ስራ 23 ከተሞች ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ ለማድረግ ታቅዶ፤ 213 አዳዲስ የገጠር ቀበሌዎችና 16 ከተሞችን በመልሶ ግንባታ በማገናኘት የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡

የዲስትሪቡሽን ኦፕሬሽን በአውቶሜሽን ቴክኖሎጂ ለማገዝና የኃይል ስርጭቱን ከአንድ ቦታ ሆኖ ለመቆጣጠር የሚያግዝ የስካዳ ሲስተም ግንባታ ሥራዎች በተመረጡ ቦታዎች የተከናወነ ሲሆን፤ የአዲስ አበባ የመቆጣጠሪያ ማዕከል በአምስት 132 ኪቮ ሰብስቴሽኖች ግንባታ በማካተት 115.06 ኪ.ሜ ኦፕቲካል ፋይበር ዝርጋታ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡

ተቋሙ የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ለማሳደግ የማሰራጫና የማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ በማከነናወን ላይ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል ከቡኢ-ቡታጅራ የ30 ኪሜ የትራንስሚሽን መስመር ግንባታ፣ የቡኢ 132/33/15 ኪ.ቮ ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ፣ የቡታጅራ 132/33/15 ኪ.ቮ ማ/ጣ የማስፋፊያ ግንባታ፣ ያቤሎ 132 ኪ.ቮ ትራንስሚሽን መስመር ግንባታ፣ የያቤሎ 132/33/15 ኪ.ቮ አዲስ የማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ፣ ጅግጅጋ-ደገሀቡር 132 ኪ.ቮ የትራንስሚሽን መስመር ፕሮጀክት (የጅግጅጋ ማ/ጣቢያ ማስፋፊያና የደገሀቡር አዲስ ማ/ጣቢያ ግንባታ) እና ጎዴ-ቀብሪደሀር የትራንስሚሽን መስመርና ዲስትሪቢዩሽን ፕሮጀክት (የቀብሪደሀር አዲስ ማ/ጣቢያ ግንባታ ስራዎች ይገኙበታል፡፡

ተቋሙ አሁን የሚስተዋለውን የሃይል መቆራረጥና መዋዥቅ ለመቀነስ በዓለም ባንክ የፋይናንስ ድጋፍ በአዲስ አበባ እና በሰባቱ ዋና ዋና የክልል ከተሞች /አዳማ፣ መቀሌ፣ ባህርዳር፣ ሐዋሳ፣ ጂማ፣ ድሬዳዋ እና ደሴ/ ተግባራዊ የተደረገው የስምንቱ ከተሞች የዲስትሪቡሽን መልሶ ግንባታና አቅም ማሳደግ ስራ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየውን የሃይል መቆራረጥ ለመቀነስና አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለመስጠት ከቻይና መንግስት በተገኘ 162.168 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብድር እየተከናወነ የሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ ዲሰትሪቡሽን መልሶ ግንባታና አቅም ማሳደግ ፕሮጀክት የኤሌክትሪክ ማሰራጫ መስመር አቅም ማሳደግና መልሶ ግንባታ ስራ አንዱ ነው፡፡  

ከዚህ በተጨማሪ ተቋሙ በሃገሪቱ የሚስተዋለወን የሃይል መቆራረጥና መዋዥቅ ለመቀነስ ከዓለም ባንክ በተገኛው 72.6 ሚሊዮን USD ብድር በአዲግራት፣ በጎንደር፣ በደብረማርቆስ፣ በወላይታ ሶዶ፣ በሻሸመኔና በሀረር ከተሞች ተግባራዊ የሚደረግ የስድስቱ ከተሞች የኤሌክትሪክ ማሰራጫ መስመር መልሶ ግንባታና አቅም ማሳደግ ፕሮጀክት ለማከናወን በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡

በ2011 በጀት ዓመት በተቋም ደረጃ 657,694 ደንበኞች የኤሌክትሪክ ኃይል ለማገናኘት ታቅዶ 195,264 ደንበኞች ማገናኘት  የተቻለ ሲሆን፣ በበጀት ዓመቱ የግብዓት ማነስ፣ የፋናንስ ዕጥረት የትራንስፎርመሮች መቃጠልና መዘረፍ እንዲሁም ከአቅም በላይ መጫንና የመሳሰሉት ተግዳሮቶች የአፈፃፀም ውጤቱን ዝቅ እንዲል ምክንያት የሆኑ እንቅፋቶች ነበሩ፡፡

ተቋሙ የገቢ አሰባሰቡንና የፋይናንስ አጠቃቀሙን ለማሻሻል በረካታ ስራዎችን ያከናወነ ሲሆን፤ ከኢነርጂ ሽያጭ 7.256 ቢሊየን ብር፣ ለረዥም ጊዜ ሳይሰበሰብ ከነበረ ውዝፍ ሂሳብ 799.30 ሚሊዮን ብር፣ ከማያገለግሉ ንብረቶች ሽያጭ 43,204,729 ብር ገቢ አግኝቷል፡፡ በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ ከተለያዩ ገቢዎች 10.123 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘት ችሏል፡፡

የኦዲት ክፍተቶችን ለመቀነስ በተለያዩ ዲስትሪክቶች በተከናወነ ኦዲት 4,890,448.22 ብር የጥሬ ገንዘብ፣ 474,326.68 ብር የንብረት በድምሩ የ5,364,774.90 ብር የዕምነት ማጉደል ተግባር የተፈፀመ ሲሆን፤  1,670,704.74 ብር ተመላሽ ተደርጓል፡፡ 3,694,070.16 ብሩ ተመላሽ መደረግ ያለበት ሂሳብ ነው፡፡

የኃይል ብክነትን ለመቀነስ 140,682 ቆጣሪዎች ላይ  ምርመራ በማድረግ 263.20 በሚሊዮን ብር በገንዘብ እና 311,951.70 MWhr ኢነርጂ ማዳን ተችሏል፡፡ ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ለማዳን የተቻለው በገንዘብ 10.8 በመቶ የጨመረ ሲሆን፤ በኢነርጂ 29.73 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡

ተቋሙ በበጀት አመቱ በርካታ ችግሮች ያጋጠሙት ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል የግብዓት አቅርቦት ችግሮች፣ የፋይናንስ ዕጥረት፣ የኤሌከትሪክ መሰረተ-ልማት ስርቆት፣ የትራንስፎርመር መቃጠል፣ የኃይልና የሃብት ብክነት፣ የቅሬታ አፈታት ስርዓት አለመጠናከርና የደንበኛ የእርካታ ደረጃ በሚፈለገው መጠን አለማደግ ይጠቀሳሉ፡፡

ተቋሙ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ የግሪዱ ሽፋን 58.56 በመቶ የደረሰ ሲሆን፤ 3.147 ሚሊዮን ደንበኞች አሉት፡፡


Print