በአሁኑ ወቅት በሀገራችን በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣውን የህብረተሰቡን የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ፍላጎት ማርካት የሚያስችል የአሰራር ስርዓት ዘርግቶ አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ ለነገ የሚተው ተግባር አይደለም፡፡12

ለዚህም አገልግሎቱን በተሻለ ሁኔታ ለማቅረብ የሚያስችሉ፣ ጊዜና ወጪን የሚቀንሱና የደንበኞችን እርካታ የሚያሳድጉ ዘመኑ ያፈራቸውን የቴክኖሎጂ መገልገያዎችንና የአሰራር ዘዴዎችን መጠቀም የደንበኛን ፍላጎት በተሻለ ደረጃ ለማርካት ከማስቻሉ ባለፈ የተቋምን አፈጻጸም በማሳደግ ረገድ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትም በአገልግሎት ዘርፉ ላይ ተግባራዊ ተደርገው ውጤታማነታቸው በአለም አቀፍ ደረጃ የተመሰከረላቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶችና የአሰራር ስርዓቶችን አጥንቶ ስራ ላይ እያዋለ ይገኛል፡፡ ከነዚህም አንዱ የቅድመ ክፍያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አንዱ ሲሆን ቴክኖሎጂው ተቋሙ ለደንበኞች የሚሰጠውን አገልግሎት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ ቀልጣፋ፣ ጊዜንና ወጪን የሚቀንስና የደንበኞችን ፍላጎት በተሻለ ለማርካት የሚያስችል ነው፡፡

የቅድመ ክፍያ የኤሌክትሪክ ቆጣሪ በስማርትና በአር.ኤፍ.አይ.ዲ. በተሰኙ ካርዶች አማካኝነት የሚሰራ ሲሆን ደንበኛው አስቀድሞ በወሰነው የገንዘብ መጠን ልክ ተመጣጣኝ የሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል ከአገልግሎቱ በተፈለገው የስራ ሰዓት በካርድ አማካኝነት መግዛት የሚያስችለው በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት ነው፡፡

ቴክኖሎጂው ደንበኛው የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታውን ከፍላጎቱ ጋር በማጣጣም አስቀድሞ እንዲያቅድ፣ በየወቅቱ ፍጆታውን እንዲለካ፣ ቀሪ የኤሌክትሪክ ኃይልና የገንዘብ መጠኑን በቀላሉ እንዲያውቅ ያስችለዋል፡፡ በተጨማሪም የንባብ ስህተትና የቆጣሪ ብልሽት ችግሮች ከሚያስከትሏቸው የቢል ማረም ውጣ ውረድና የተከማቸ የክፍያ ዕዳ ያድናል፡፡

ለተቋሙም የፍጆታ ክፍያን አስቀድሞ ለመሰብሰብ በማስቻል ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከማበርከቱ ባሻገር ለቆጣሪ ንባብ ይውል የነበረውን ጊዜ፣ የሰው ሀይል፣ ወጪ እንዲሁም ቆረጣና ቅጠላን በማስቀረት በኩል ትልቅ ጠቀሜታ ያበረክታል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአገልግሎት አሰጣጡን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ ከሚያዚያ 2011 ዓ.ም ጀምሮ የኢ.አር.ፒ ሶፍትዌርን በሀገር አቀፍ ደረጃ በኔትወርክ በተሳሰሩ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላቱ ስራ ላይ አውሏል፡፡ ይህም ቀድሞ በውስን ማዕከላት ብቻ ይሰጥ የነበረውን የቅድመ ክፍያ አገልግሎት አድማስ በማስፋት ደንበኞች በየትኛውም የአገልግሎቱ ማዕከል በመሄድ አገልግሎቱን እንዲያገኙ አስችሏል፡፡

በተጨማሪም አገልግሎቱ በኢ.አር.ፒ ሶፍትዌር አማካኝነት የሚሰጥ በመሆኑ በዋናው መ/ቤት፣ በክልል የአገልግሎት ጽ/ቤቶችና በዲስትሪክቶች የሚገኙ የስራ ኃላፊዎች የቅድመ ክፍያ አገልግሎት አሰጣጥ ሂደትን በየዕለቱ መከታተል የቻሉ ሲሆን በዚህም አስፈላጊ ውሳኔዎችንና ማስተካከያዎችን በወቅቱ ለመስጠት አስችሏቸዋል፡፡ ይህም በአገልግሎት አሰጣጡ ዘርፍ ሊኖር የሚገባውን የአሰራር ግልፀኝነት እንዲሰፍን ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡

በአሁኑ ወቅት የቅድመ ክፍያ አገልግሎትን ለማስፋፋት ለአገልግሎቱ ግብዓት የሚሆኑ የቆጣሪ፣ የካርድና የካርድ ሪደር አቅርቦትን አስተማማኝ ለማድረግ ጥረት በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡

የቅድመ ክፍያ አገልግሎት ለማግኘት የሚፈልግ አዲስ ወይም ነባር ደንበኛ አቅራቢያው በሚገኝ የአገልግሎቱ ማዕከል በመቅረብና አስፈላጊ ማስረጃዎችን ማለትም መታወቂያ፣ ማመልከቻ፣ የቀበሌ ቤት ከሆነ ከቀበሌ የተሰጠ የድጋፍ ማስረጃ በማቅረብና አስፈላጊውን ክፍያ በመፈፀም አገልግሎቱን ማግኘት ይችላል፡፡

የቅድመ ክፍያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ደንበኞች ለአገልግሎቱ የሚጠቀሙበትን ካርድ ጉዳት እንዳይደርስበትና እንዳይጠፋ በማድረግ በጥንቃቄ ሊገለገሉበት ይገባል፡፡ ካርዱን ለማስቀየር የሚፈልግ ደንበኛ አገልግሎቱን ለማግኘት የተዋዋለውን ውል ወይም የሀይል ግዢ የፈፀመበትን ደረሰኝና 152 ብር (አንድ መቶ ሀምሳ ሁለት ብር) በመያዝ ውል ወደ ፈጸመበት ማዕከል በመሄድ አገልግሎቱን ማግኘት ይችላል፡፡

ቀድሞ የተሞላ የአገልግሎት ሂሳቡ ሳያልቅ ቆጣሪው አገልግሎት መስጠት ቢያቆም ደንበኛው ወደ አቅራቢያው የአገልግሎቱ ማዕከል በመሄድና ማስነሻ በማስሞላት አገልግሎቱን መልሶ ማግኘት የሚችል ሲሆን በአገልግሎት ወቅት ችግር ሲገጥም ካርድ የሚሞላውን ኦፕሬተር በማናገር ችግሩ እንዲፈታ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ካርዱ ተሞልቶ ነገር ግን  የኔትወርክ ችግር ቢያጋጥም የአገልግሎት ውል በተፈፀመበት ማዕከል በመገኘት ችግሩን ማስተካከል ይቻላል፡፡

የቅድመ ክፍያ ቆጣሪ አገልግሎት በ1999 ዓ.ም በውስን የሀገሪቱ ከተሞች የተጀመረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱን ማስፋት በመቻሉ በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች፣ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ፣ ትግራይ፣ ሶማሌ፣ አፋርና ሐረር ክልሎች በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች አገልግሎቱ እየተሰጠ ይገኛል፡፡ በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት 569,460 ደንበኞች የቅድመ ክፍያ አገልግሎት ተጠቃሚ ናቸው፡፡