የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአሶሳ ከተማ ከ15 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ አድርጎ ያስገነባውን ባለ ሁለት ፎቅ የቢሮ ህንፃ ጥር 16 ቀን 2012 ዓ.ም በይፋ አስመርቋል፡፡merkat

የክልሉ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ከበደ ምርቃቱን አስመልክቶ እንደገለፁት አገልግሎት አሠጣጥ ሂደት ውስጥ ለሠራተኛው እና ለተገልጋይ ህብረተሰብ ምቹ የሆነ ቢሮ ማግኘት ቀዳሚ ጉዳይ መሆኑን አንስተው፣ ህንፃው ሲገነባ ለዜጎች የስራ እድል ከመፍጠሩም ባሻገር በዓመት ሪጅኑ ለቤት ኪራይ የሚያወጣውን 396,000 ብር ማስቀረት እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡

አቶ ካሳሁን አክለውም ህንፃውን በተቋሙ ግንባታ ክትትልና ቁጥጥር ቢሮ መገንባቱ የጥራት ደረጃውን ከመጠበቅ ባሻገር 2,876,770 ብር ማዳን መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡
ሪጅኑ እስካሁን ጋራዥ ያልነበረው መሆኑን አንስተው ለትንንሽ ብልሽት ምክንያት መኪኖቹን ለማሰራት ወደ አዲስ አበባ ልከው እንደሚያስጠግኑና ለከፍተኛ ወጭ፣ ለጊዜ ብክነት፣ ለተሸከርካሪ አጠቃቀም ውጤታማነት መጓደል መጋለጣቸውንም አስታውሰዋል፡፡84713435 3050895701589189 3925834308815683584 o

ከህንፃው ግንባታ በተጨማሪም ለመካከለኛ ጥገና የሚውል ጋራዥ፣ ለትራንስፎርመር የሚውል ወርክ ሾፕ፣ የህፃናት ማቆያ ተገንብተው መጠናቀቃቸውን አቶ ካሳሁን ገልፀዋል፡፡

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመሰረተ ልማትና ኢንቨስትመንት አማካሪ አቶ ኢዶሳ ጎሹ በበኩላቸው የልማትና የእድገት ውጤት ከሆኑ የመሰረተ ልማት አውታሮች መካከል የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ በአሁኑ ጊዜ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲፋጠንና ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል፡፡

ኤሌክትሪክ በክልሉ ብሎም በከተማ እና በገጠር ባሉ በእያንዳንዱ ዜጋ ቤት ውስጥ በመድረስ የህብረተሰቡን ፍትሃዊ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን አቶ ኢዶሳ አድንቀዋል፡፡

ተቋሙ የራሱን ህንፃ መገንባቱ አገልግሎቱን አሰጣጡን ለማሳለጥና የአሰራር ስርአቱን ለማዘመን ለደንበኞችን የተቀላጠፈና አገልግሎት ከመስጠት አኳያ በተለያዩ የሰራ ክፍሎች ምቹ የስራ አካባቢን መፍጠር የሚያስችልና የቢሮ ኪራይ ወጪ ከመቀነስም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አሰፈፃሚው አቶ ሽፈራው ተሊላ ናቸው፡፡

አብዛኛው የዲስትሪክትና የሪጅን ቢሮዎች በኪራይ ያሉ መሆናቸውን ገልፀው በዓመት በአማካኝ ከ75 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ይወጣል ብለዋል፡፡
ይህንንም የኪራይ ወጪ ለመቀነስ በተያዘው በጀት ዓመትና በቀጣይ አምስት ዓመታት እስከ 29 የሚደርሱ ቢሮዎችን ለመገንባት እቅድ ይዘው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ዋና ስራ አስፈፃሚው የገለፁት፡፡

በዕለቱም ዋና ስራ አስፈፃሚው የሃገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ጽ/ቤት የሚሆን የቢሮ ህንፃ በሪጅኑ ግቢ ውስጥ ለማስገንባት የመሰረተ ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡

በምርቃቱም የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመሰረተ ልማትና ኢንቨስትመንት አማካሪ አቶ ኢዶሳ ጎሹ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ፣ የክልል ምክትል ስራ አስፈፃሚዎች፣ የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች እና የከፍተኛና መካከለኛ ኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች እንዲሁም የተቋሙ ሰራተኞች ተገኝተዋል፡፡