የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት፣ የተቋሙን አደረጃጀትና የስራ ፍሰት ለማስተካከል እንዲሁም የቴክኒክ ልህቀትን እውን ለማድረግ የሚያግዘው የኢንተርፕራይዝ ሪሶርስ ፕላኒንግ (ERP/SAP) ፕሮጀክት በመገንባት ቆይቶ፤ አሁን ትግበራው ጀምሯል፡፡ERP2

የፕሮጀክቱ ግንባታ የተጀመረው አለም አቀፍ ተቀባይነት ካለውና ቴክ ማሂንድራ ከተሰኘው የህንድ ኩባንያ ጋር የውል ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ነው፡፡ የፕሮጀክቱ ስምምነት የተፈረመው ጥቅምት ወር 2008 ዓ.ም ሲሆን፤ በይፋ ስራው የተጀመረው ደግሞ ጥር 28 ቀን 2008 ዓ.ም ነው፡፡

የኮንትራት ውል ስምምነቱ አጠቃላይ ወጪ 58.90 ሚሌዮን የአሜሪካን ዶላር ሲሆን፤ የኮንትራቱ የመጀመርያ ምዕራፍ /ለትግበራና ስታንዳርድ ዋራንቲ/ የተከናወነው ከአለም ባንክ በተገኝ 46.04 ሚሊዮን ዶላር ብድር ነው፡፡  የሁለተኛ ምዕራፍ /የላይሰንስና የሜይንተናነስ ሳፖርት/ ስራ ደግሞ በ12.86 ሚሌዮን የአሜሪካን ዶላር በተቋሙ በጀት ተይዞለት ለተከታታይ 3 ዓመታት የሚከናወን ይሆናል፡፡

የኢ.አር.ፒ ፕሮጀክት የስራው ስፋትና ውስብስብነት (Scope & Complexity) ተሳቢ ባደረገ መልኩ በፕሮግራም ደረጃ እንዲመራ እና በስሩ ሁለት ፕሮጀክቶች ማለትም የአፕሌኬሽንና የኢንፍራስትራክቸር ፕሮጀክት ተደራጅቷል፡፡

በአ.አር.ፒ ፕሮጀክት የተከናወኑ ዋና ዋና ስራዎችን ስንመለከት ፡- ከዋናው መ/ቤት እስከ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት የሚሰሩ ሰራተኞች ሴንትራሊይዝድ የኢንቴርኔት እና የኢሜይል አገልግሎት ተዘርግቷል፡፡ ደረጃውን የጠበቀ ዋናው የመረጃ ማእከል (Primary Data Center) እና የተለዋጭ (Disaster Recovery Data Center) የመረጃ ማእከል ተግንብቷል፡፡

በ11 የሪጅን ፤ 28 የዲስትሪክት ቢሮዎች እና 382 የአገልግሎት መስጫ ማእከላት የኔትዎርክ (LAN & WAN) ትግበራ ተከናወኗል፡፡ በአንዴ ጊዜ 80 ደንበኞችን ማስተናገድ የሚችል የደንበኞች ጥሪ ማእከል እና የተቋሙ የውስጥ ሰራተኞች ጥሪ ማስተናገድ የሚያስችል የIT Help Desk System ተግንብቷል፡፡ የአውቶማቲክ ሜትር ሪዲንግ (AMRS) ሲሰተም ትግበራ በ35 ሰብስቴሽኖች ላይ ማለትም በአዲስ አበባ እና በዙሪያ በሚገኙ ሰብስቴሽኖች፤ በአዳማ ፤ በባህር ዳር፤ በመቐለ፤ በሀዋሳ ፤ በሀረሪ፣ በዴሬዳዋ ትግበራ የተሰራ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 452 አውቶማቲክ ኢነርጂ ሜትርና 39 DCU ተተግብሯል፡፡

የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ጎ-ላይቭ ሚያዚያ 01 ቀን 2011 ዓ.ም ስድስት የECC ሞጁሎችን ማለትም የፋይናንስና ኮንትሮል፤ የሰው ሀብትና ፔሮል፤ የንብረት አስተዳደርና የእቃ ግምጃ ቤት፤ የኢንተርፕራይዝ አሴት አስተዳደር፤ የፕሮጀክት አስተዳደር እና የጥራት አስተዳደር በሁሉም የተቋሙ የስራ ክፍሎች ላይ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡

በሁለተኛው ምዕራፍ ጎ-ላይቭ የደንበኞች አገልግሎት፤ የጥሪ ማዕከል፤ የንባብና የቢሊ እንዲሁም ገንዘብ ስብሰባ ጋር የተገናኙ ሞጁሎች ከግንቦት 2011 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አባባ ሪጅን፤ ከሐምሌ 07 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በ6 ሪጅኖች ማለትም አማራ፤ ትግራይ፤ ጋምቤላ፤ ቤንሻንጉል፤ ዴሬዳዋ እና ሀረሪ የሪጅን ቢሮዎች ላይ ስራ ላይ ውሏል፡፡ በተመሳሳይ መልክ ከነሀሴ 07 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለተቀሩት 4 ሪጅኖች ላይ ማለትም በኦሮምያ፤ ደቡብ ፤ ሶማሌና አፋር ላይ ተደርጓል፡፡

በአጠቃላይ በኢ.አር.ፒ ፕሮጀክት ትግበራ ጋር ተያይዞ የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች የተከናወኑ ሲሆን፣ ከ4000 በላይ የፕሮጀክት ቡድን (የኮር፤ የሻምፒዮን) እና የሲሰተም ተጠቃሚ ክፍሎች (End Users) የተለየዩ የቴክኒካል እና የሲሰተም አጠቃቀም ስልጠና ተከናውኗል፡፡

ይህ ፕሮጀክት በመተግበሩ ተቋሙ ላይ የተፈጠረው አዎንታዊ ለውጡ ከፍተኛ ሲሆን፣ አሁን ባለው የትግበራ ደረጃ በተቋሙ ውስጥ የሚሰራው ስራ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ሲስተም መሰረት ያደረገ ሆኗል፡፡ ይህ በመሆኑ የተቋሙ የለት ተለት ስራዎች በሲስተም የመስራት፣ የማቴሪያል እና የፋይናንስ እንቅስቃሴዎች መከታተልና መቆጣጠር የሚያስችል ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ተቋሙ ካስቀመጠው አሰራር፤ መመርያና ፖሊሲ ውጭ የተሰሩ ስራዎችን ሲስተሙን በመጠቀም መከታተልና የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

ሲስተሙ በአጠቃላይ የሚያስገኘው ጥቅሞች

የተቋሙ መረጃዎችን ወጥ በሆነ መንገድ ለማደራጀት፣ በተጨባጭ መረጃ ላይ ተመርኩዞ ውሳኔዎችን ለመወሰን፣ የስራ እቅድና አፈፃፀም ሪፖርት ከተቋሙ አመታዊ ፋይናንስ ዕቅድ፣ በጀትና ስራ አፈፃፀም ቀመር አንፃር እንዲናበብ ለማደረግ፤ የተደራጀና የተሟላ የአቅርቦት አስተዳደር ስርዓት እንዲኖር፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የተቀላጠፈና ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት፣ ትክክለኛ የሆነ የቆጣሪ ንባብና የንባብ መረጃ አስተዳደር እንዲኖር ለማድረግ፣ የቢል ትክክለኛነትና ውጤታማነት ደረጃን ለማሻሻል፣ ደንበኞች የተጠቀሙበትን ሂሳብ መረጃ በወቅቱ እንዲያገኙ፣ የፍጆታ ሂሳብ በተለያዩ የመክፈያ መንገዶች ለመፈፀም፣ ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ስራ ለማከናወን፣ የመፈፀም አቅምን ለማሳደግ እና ከአሰራር ውጪ የሚፈጠር ችግርን ለመቀነስ ይጠቅማል፡፡

በፕሮጀክት ትግበራ ወቅት ያገጠሙ ችግሮች

የአደረጃጀት መለዋወጥ፤ የተቋሙ መረጃዎች በሚፈለገው መልክ ተደራጅተው እና ተዘጋጅተው ያለመኖር፤ የኮሚፕዩተር ክህሎት ያለው የሰው ሃይል ማነስ፤ ስልጠና የወሰዱ ተጠቃሚዎች ሲስተሙን ተጠቅሞ ስራ ለመስራት ተነሳሽት ማነስ፤ የተወሰኑ ደንበኞች መረጃ በተለያዩ ምክንያች ወደ አዲሱ ሲስተም ባለመግባቱ ቢል አለመውጣት ችግሮች በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡