የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ስታንዳርድና የቋሚ ንብረት ምዝገባ፣ ዋጋ ትመና ፕሮግራም በማቋቋም የተቋሙን የንብረት አያያዝ መረጃ አለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለመያዝ እየሰራ ይገኛል፡፡advertisingonpolforbiden

ለዚህም የIFRS ስርዓትን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ በማድረግ የተቋሙን ንብረት በመቁጠርና በመመዝገብ አሁን ባለው ወቅታዊ ዋጋ ክለሳ በማድረግ ተቋሙ ያለውን ሃብት በትክክል እንዲያውቅ ለማድረግ የሚረዱ ስራዎችን እየተሰራ ነው፡፡

እስካሁንም የመካከለኛ ቮልቴጅ ምሰሶ፣ ትራንፎርመርና ተያያዥ የዲስትሪቡዩሽን መስመር መረጃዎች ተሰብስቦ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ በአሁኑ ጊዜ የዝቅተኛ ቮልቴጅ መስመር ምሰሶ መረጃ እየተሰበሰበ ይገኛል፡፡ መረጃው ሲሰበሰብ በዋናነት የምሰሶዎች መለያ ቁጥር እየተሰጠ በላዩ ላይ ይለጠፋል፡፡

የምሰሶ መለያ ቁጥር መስጠቱ ዋና አላማ መስመሩን ዲጅታይዝ ለማድረግና የደንበኞች አገልግሎት ስራዎችን ለማሻሻል ሲሆን፣ የቆጣሪና የደንበኞች መረጃ በሚሰበሰብበት ጊዜ እነዚህ የምሰሶ መለያ ቁጥሮች መነሻ ሆኖ ያገለግላል፡፡

ነገር ግን ተቋሙ ይህንን ስራ በአግባቡ እንዳያከናውኑ እንቅፋት ከሆኑበት ጉዳዮች በዋናነት በኤሌክትሪክ ምሰሶዎቹ ላይ የሚለጠፉና የሚንጠለጠሉ የማስታወቂያ ወረቀቶች ይጠቀሳል፡፡ በተለይ ደግሞ ለምሰሶዎቹ መለያ ቁጥር ከተሠጠ በኃላም እላዩ ላይ የማስታወቂያ ወረቀቶች እየተለጠፈበት ይገኛል፡፡

ይህም የምሰሶ ቁጥር ለመስጠት እንቅፋት ከመሆኑም በላይ ተቋሙ እያከናወነው ባለው የዲጂታይዝ ሥራ ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠር ነው፡፡
ይሁን እንጂ ከፍተኛ የህዝብ ሃብት ፈሶባቸው እየተገነቡ በሚገኙ በነዚህ የኤሌክትሪክ ተሸካሚ ምሰሶች ላይ ተለጥፎባቸው ይታያሉ፡፡
በመሆኑም ይህንን ህገ ወጥ ተግባር የምትፈፅሙ አካላት፤ በተቋሙ የዲስትሪቡዩሽን ኔትወርክ ምሰሶዎች ላይ ምንም ዓይነት የማስታወቂያ መልዕክት መለጠፍ፣ ባነሮችና መሰል ወረቀቶች ማንጠልጠል በፍፁም የማይፈቀድ መሆኑን አውቃችሁ፤ ከዚህ በፊት የለጠፋችሁና ያንጠለጠላችሁ ማስታወቂያዎች በአስቸኳይ እንድታነሱ እናሳስባለን፡፡

በኤሌክትሪክ ተሸካሚ ምሰሶች ላይ ማስታወቂያዎች፣ ባነሮችና ሌሎች ጽሑፎች መለጠፍ ወንጀልና በህግ የሚያስጠይቅ መሆኑን ተገንዝቦ፣ ማንኛውም ግለሰብ ወይም ድርጅት መሰል ተግባር ከማከናወን እንዲቆጠብ እንጠይቃለን፡፡
ሆኖም ይህንን ተላልፈው በሚገኙ ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ ተቋሙ በህግ ተጠያቂ እንደሚያደርግ አስቀድሞ ያሳውቃል፡፡