የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰቱ የኤሌክትሪክ መቆራረጥንና መዋዠቅን ለመቀነስ እንዲሁም ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

ነገር ግን ተቋሙ ተልዕኮውን እንዳያሳካ አንዳንድ ኃላፊነት የጎደላቸው አካላት ከገቡት የአገልግሎት ውል ውጭ በህገ ወጥ መንገድ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚጠቀሙ ደርሰንበታል፡፡88236431 3132027216809370 6083932521811148800 n

በተለይም በኪራይ ቤት ውስጥ ኃይል በመጠቀም የተለያዩ ስራዎችን በሚሰሩ አካላት ከፍተኛ የኃይል ስርቆት እንደሚፈጸም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በእነዚህ አካላት ላይ ክትትል በማድረግ አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ የምንወስድ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ከተቋማችን ጋር ኤሌክትሪክ ለመጠቀም የአገልግሎት ውል ገብታችሁ ቤት የምታከራዩ ደንበኞቻችን በቤቱ ውስጥ ለሚፈጸም ኃይል ሰርቆትና ውዝፍ የፍጆታ ክፍያ ኃላፊነት ያላባችሁ መሆኑን በመገንዘብ ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር እንድታደርጉ እናሳስባለን፡፡

በተመሳሳይ መልኩ የቤት ግዥ የምትፈጽሙ ደንበኞችም የቤት ግዥና የስም ዝውውር ከመከናወኑ በፊት በአቅራቢያችሁ ከሚገኝ የአገልግሎት መስጫ ማዕከል በአካል በመቅረብ ውዝፍ የኃይል ፍጆታ ዕዳዎችን ማጣራት፣ ቆጣሪው ከወንጀል ድርጊት የፀዳ መሆኑን ማረጋገጥና ውላችሁን በድጋሚ ማደስ እንደሚገባችሁ በአፅንኦት እናሳስባለን፡፡

ይህን ባለማድረግ የሚመጣ ቀድሞ የነበረ የፍጆታ ሂሳብ ዕዳም ሆነ ስርቆት እንዲሁም የወንጀል ጥያቄ የቤቱ ባለቤት እንደሚሆን ተቋሙ እያሳወቀ፤ ሁሉም የተቋሙ ደንበኛ አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ በድጋሚ እንገልፃለን፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል መስረቅ፣ በህገወጥ መንገድ ከሌላ መስመር ጋር ማገናኘት፣ መስመሩን ማሰናከል ወይም የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲሰረቅ ከሌላ መስመር ጋር እንዲገናኝ ወይም መስመሩ እንዲሰናከል ማድረግ በሃገሪቱ የኢነርጂ አዋጁ ቁጥር 810/2006 መሰረት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ወይም እስከ ብር 20,000 በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ወይም በሁለቱም የሚያስቀጣ ወንጀል ነው፡፡