በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ የሚፈፀሙ ጉዳቶችና ስርቆቶች በተቋሙ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ከማሳደራቸው በተጨማሪ በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያመጡት ኪሳራ ከፍተኛ ነው፡፡

በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ላይ የሚፈጸም ስርቆትን ለመከላከልና ተፈጽሞ ሲገኝ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል የኢነረጂ አዋጅ ያለ ሲሆን፤ በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ላይ ስርቆት የሚፈጽም ወይም ጉዳት የሚያደርስ አካል በኢነርጅ አዋጅ 810/2006 አንቀጽ 26 እና 29 ተጠያቂ ይሆናል፡፡theft

ኢነርጅ አዋጅ 810/2006 አንቀጽ 26 በማመንጫ፣ ማሰተላለፊያ ወይም ማከፋፈያ ተቋማት ላይ ጉዳት ያደረሰ ማንኛውም ሰው ከ5 እስከ 15 አመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ወይም እስከ ብር 50 ሺህ የሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ወይም በሁለቱም እንደሚቀጣ ይደነግጋል፡፡

እንዲሁም ማናቸውንም የኤሌክትሪክ መስመር ተሸካሚ አካላትን ያለያየ፣ የሰረቀ ወይም በማለያየቱና በስርቆቱ የተባበረ እና በኤሌክትሪክ መሰመሮች ላይ ሆን ብሎ ወይም በግዴለሽነት ጉዳት በማድረስ ያቋረጠ እስከ 5 አመት የሚደርስ ጽኑ እስራት ወይም ከብር 25 ሺህ ባልበለጠ የገንዘብ መቀጮ ወይም ሁለቱንም እንዲቀጡ ህጉ ይደነግጋል፡፡

በባለፈው ስድስት ወራት በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ዝርፊያ ሲያካሂዱ የተገኙ 18 ግለሰቦችም ክስ ተመስርቶባቸው ፍርድ አግኝተዋል፡፡
በዚህም መሰረት በአንድ ሰው ላይ 10 ዓመት፣ በ6 ሰዎች ላይ 9 ዓመት፣ በ6 ሰዎች ላይ 4 ዓመት ተኩል እንዲሁም በ5 ሰዎች ላይ 2 ዓመት ተፈርዶባቸዋል፡፡

በመሆኑም አውቀውም ይሁን ባለማወቅ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ ስርቆት ወይም ጉዳት የሚያደርሱ ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ተቋሙ ያሳስባል፡፡
ህብረተሰቡም የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶችን እንደራሱ ንብረት አድርጎ በመንከባከብና በመጠበቅ በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ስርቆቶችን ሊከላከል ይገባል፡፡

የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን የሚነካኩ ግለሰቦች ሲያጋጥሙ በተቋሙ የተመደቡ ሠራተኞች መሆናቸውን የሚገልፅ መታወቂያ መያዛቸውን በመጠየቅ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግና በአከባቢው በሚገኝ የአገልግሎት መስጫ ማዕከል በአካል በመሄድ ማሳወቅ ወይም በ905 ነፃ የጥሪ ማዕከል በመደወል ጥቆማ መስጠት ያስፈልጋል፡፡