በደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች በተቋማዊ የለውጥ ስራዎችና በአዲሱ ታሪፍ ማስተካከያ አተገባበር ላይ ውይይት ተካሄደ

47576840 2271744019504365 6183732121362759680 n

በደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች ኤሌክትሪክ አገልግሎት ቢሮዎች ስር ከሚገኙት ሃዋሳ፣ ሆሳዕና፣ ወላይታ ሶዶ፣ አርባ ምንጭ፣ ባሌ ሮቤና ሻሸመኔ ዲስትሪክቶች የተውጣጡ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላትና ሳተላይት ጣቢያዎች ሃላፊዎች፣ ሱፐርቫይዘሮችና ቆጣሪ አንባቢዎች ጋር በቀልጣፋ አገልግሎት አስጣጥ፣ በተቋማዊ ለውጥ ትግበራና በአዲሱ የታሪፍ ማስተካከያ ትግበራ ዙሪያ ዛሬ በሃዋሳ ከተማ ውይይት ተካሂዷል፡፡

ውይይቱን የከፈቱት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ እንደተናገሩት ተቋሙ የተጣለበትን ሀገራዊ ተልዕኮ ለመወጣት በርካት ለውጦችን በማካሄድ ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከሚከናወኑት ተግባራት መካከል የተቋሙን የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻልና ማዘመን እንዲሁም ግልፀኝነትና ተጠያቂነት የማስፈን ተግባራት ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ተቋሙ ካለበት ችግር ለመላቀቅ ተቋማዊ ልውጡን ዕውን ማድረግና የፋይናንስ አቅሙን ማሳደግ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

በመድረኩ ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡት አቶ እሱባለው ጤናው፣ የተቋሙ የለውጥና መልካም አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እንደገለፁት በተቋሙ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የማሰራጫ መስመሮች ማርጀት፣ የዲስትሪቡሽን ዕቃዎች ዕጥረት፣ ገቢን አማጦ አለመሰብሰብ፣ በአለምና አገር ኣቀፍ ሁኔታዎች ምክንያት ከገቢ ጋር ልተመታጠነ ወጪ መኖር፣ ከፍተኛ የሀይል ብክነት፣ የትራንስፖርት አቅርቦት ውስንነት፣ በቴክኖሎጂ ያልታገዘ አሰራር፣ አነስተኛ የአገልግሎት ታሪፍ መኖር የዘርፉ ቁልፍ ተግዳሮቶች መሆናቸውን አመለክተዋል፡፡

ይህም በመሆኑ የሀይል መቆራረጥና መዋዥቅ፣ የአስቸኳይ ጥገና ቀልጣፋ አለመሆን፣ የአዳዲስ ሃይል ፈላጊ ደንበኞች ጥያቄ በአፋጣኝ ያለመመለስ፣ ሌሎች የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲከሰቱ መንስኤ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም ወጪን ያማከለ የአገልግሎት ገቢ እንዲኖር ማስቻል፣ ያረጁና ዝቅተኛ አቅም ያላቸውን የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ማሻሻልና አቅማቸውን ማሳደግ፣ የህብረተሰቡን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ አዳዲስ የኤሌክትሪክ መስመሮን መገንባት፣ የግብዓት አቅርቦትን አስተማማኝ ማድረግ፣ ሀይል ጠያቂ ደንበኞችን በቅልጠፍና ማስተናገድ፣ ወቅቱ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ማድረግና መልካም አስተዳደርን ማስፈን ችግሮቹን ለመቅረፍ መፍትሄ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የተቋሙ የፋይናንስ አቅምም ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎችም የሰራተኞች ጥቅማጥቅም በተመለከተ፣ የግብዓት አቅርቦት፣ የውዝፍ ሂሳብ አሰባሰብ፣ የማይሰሩ ቆጣሪዎች ቅየራ፣ ሲስተም ያልገቡ ደንበኞች መኖር፣ የሰው ሀይል ክፍተት፣ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች ላይ ጥያቄዎች አንሰተው በተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ምላሽ ተሰጥቶበታል፡፡

ተቋሙ የሰራተኞች ጥቅማጥቅም ለማስጠበቅ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን፤ ሆኖም ገቢን ለማሳደግ መላው ሰራተኛ ተቋማዊ ለውጡንና የታሪፍ ማስተካከያውን በንቃት ማስፈፀም እንደሚኖርበት አስገንዘበዋል፡፡

ውዝፍ የፍጆታ ሂሳብ አሰባሰብ፣ የቆሙ ቆጣሪዎችን መቀየርና ወደ ሲስተም ያልገቡ ደንበኞችን ማስገባትን በተመለከተ ከወራት በፊት በሁሉም የክልል ቢሮዎች ስር ባሉ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት ስራው ሲከናወን መቆየቱን ጠቅሰው ያላጠናቀቁ ማዕከላት በቀሪው ጊዜ በአስቸኳያ ማከናወን እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ ውዝፍ ሂሳብ አከፋፈልን በተመለከተ በቀጣይ ወጥ የሆነ አሰራር ይዘረጋልም ብለዋል፡፡

የግብዓት ችግሮችን ለመቅረፍ የተለያዩ ስራዎች በመከናወን ላይ መሆኑን የጠቀሱት ስራ አስፈፃሚው ችግሩ በጥቂት ወራት ውስጥ ሲቃለል ከፍለው በመጠባበቅ ላይ ያሉ ደንበኞችን እስከ ሰኔ ወር ለማስተናገድ ጥረት እንደሚደረግ ጠቅሰዋል፡፡ የሰው ሀይል ክፍተቱን በዕድገትና ቅጥር ለመቅረፍ ጥረት እንደሚደረግ ጠቁመው የአቅም ግንባታውም ጎን ለጎን መከናወን አለበት ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በውይይቱም ላይ የተቋሙ ሀላፊዎች ከሰራተኞች የተነሱትን ሃሳቦች በማስመልከት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም ተሳታፊዎች የተቋሙን ሁለንተናዊ ዕደገት ለማረጋገጥ የተጣለባቸውን አደራ በታማኝነት ለመወጣት ቃል በመግባት ውይይቱ ተጠናቋል፡፡

47495124 2271744806170953 5982056550385057792 n


Print