በመጪው ገና በዓል የኃይል መቆራረጥና መዋዠቅ ችግር እንዳይኖር ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል

Image may contain: text

ህብረተሰቡ በዓሉ በሰላምና በደስታ እንዲያሳልፍ በበዓላት ከሚኖረዉ ከፍተኛ የሀይል ፍልጎት አኳያ ሊያጋጥም የሚችለውን የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና መዋዠቅ በዘንድሮ የገና በዓል እንዳይከሰት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በኩል አስፈላጊ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ ተቋማችን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ጋር በመሆን በአገር አቀፍ ደረጃ በዓሉን ተከትሎ ለሚፈጠረው የኃይል መቆራረጥና መዋዠቅ አፋጣኝ መፍትሔ የሚሰጥ የጋራ ስታንድ ባይ ኮሚቴ ከወዲሁ አቋቁሟል፡፡

የበዓሉ ቀን ከመድረሱ በፊት ችግሩ ይከሰትባቸዋል የተባሉ አካባቢዎች በመለየት የተለያዩ የመልሶ ግንባታ፣ አቅም የማሳደግ፣ የጭነት ማመጣጠንና የቅድመ መከላከል ጥገና ሥራዎች በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡ በበዓሉ ቀንም የሚፈጠሩትን የሃይል መቆራረጥ በአፋጣኝ ለመፍታት የሚያስችሉ የአስፈላጊ ግብዓቶች አቅርቦትም የማሟላት ሥራ ተከናውኗል፡፡

ሆኖም ከበዓሉ ጋር ተይያዞ በኤሌክትሪክ ኔትዎርኩ ላይ ከፍተኛ የኃይል መጨናነቅ ሊከሰት ስለሚችል ከግሪድ ኃይል የሚታገኙ የድንጋይ ወፍጮ፣ የፕላሳቲክ፣ የጨርቃ ጨርቅ፣ የብረታ ብረት፣ የቆዳና ሌዘር፣ የኬሚካል፣ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች እንዲሁም ሌሎች የከፍተኛና የመካከለኛ ኃይል ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎች ከታህሳስ 28 ቀን 2011 ዓ.ም ከንጋቱ 12፡00 ጀምሮ እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2011 ዓ.ም ከንጋቱ 12፡00 ድረስ ኃይል ቀንሳችሁ እንድትጠቀሙ የተለመደ ትብብራቸሁን እንጠይቃለን።

በኅብረተሰቡ በኩልም ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ነገሮች አስቀድሞ በማዘጋጀት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ጭነት በማይበዛበት ሰዓት በተለይ ከምሽቱ 3፡00 እስከ ሌሊቱ 12፡00 ባለው ጊዜ በመጠቀም ከቀን በተሻለ የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት ይቻላል፡፡ የሚፈጠረውም የሀይል መጨናነቅ ይቀንሳል፡፡

በበዓሉ የቅድመ ክፍያ የቆጣሪ አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞቻችን ካርድ መሙላት ከፈለጋችሁ በዋዜማው እስከ ምሽቱ 1፡00 ድረስ አገልግሎቱ በሚሰጡ ሁሉም ማዕከላቶች ማግኘት እንደምትችሉ እንገልፃለን፡፡ እንዲሁም ከ50 ኪዋ በላይ የሚጠቀሙ ደንበኞች በአዲሱ ታሪፍ ማስተካከያ መሰረት የሚሰራላቸው በመሆኑ፤ የምትሞሉት የገንዘብ መጠን እንድታሻሽሉና ኃይል ቆጥባችሁ እንድትጠቀሙ እንመክራለን፡፡

አሌክትሪክ በሚቋረጥበት ጊዜ ከሥራ ሰዓት ውጪ ጥገና ለማከናወን የተቋማችን መታወቂያ የያዙ ባለሞያዎቻችን በተለያዩ አካባቢዎች ሊንቀሳቀሱ ስለሚችሉ፤ ህብረተሰቡ ይህንን ተገንዝቦ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግላቸውም እንጠይቃለን፡፡ ደንበኞቻችን ከኤሌክትሪክ ጋር በተገናኘ ማንኛውም ዓይነት መረጃ ሲፈልጉ ወዲውኑ በአካል ወደ አቅርቢያ የአገልግሎት መስጫ ማዕከል በመሄድ እና በአማራጭነት በአዲስ አበባ የሚገኙ ደንበኞቻችን በነፃ የጥሪ ማዕከላችን 905 በመደወል ማሳወቅ ትችላላችሁ፡፡


Print