ጣሪ ንባብ መመዝገቢያ መሳሪያ - ሌላው የቴክኖሎጂ አማራጭ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚሰጠው አገልግሎት አለም ዓቀፍ መስፈርትን በማሟላት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ደንበኞችን እርካታ ለማሳደግ በየወቅቱ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ ሆኖም በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች በደንበኛው ላይ ከሚያስከትሉት ጫና ባሻገር በተቋሙ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠራቸው አልቀረም፡፡ በተለይ የአገልግሎቱን ጥራትና ቅልጥፍናን በተመለከት ደንበኞች የሚያነሷቸው ቅሬታዎች ትኩረት ከሚሹት ጉዳዮች መካከል ግንባር ቀደሞቹ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱ አስተማማኝና ፍትሀዊ ይሆን ዘንድ ደንበኞች ወርሃዊ የፍጆታ ሂሳባቸውን በቅርቡ ተግባራዊ በተደረገው የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ትግበራ መሰረት በአቅራቢያቸው ባለ የተቋሙ የአገልግሎት መስጫ ማዕከል በመገኘት መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከደንበኞች የሚሰበሰበው ገቢም አገልግሎቱን ተደራሽና ቀልጣፋ እንዲሆን በማድረግ ረገድ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል፡፡meterreding

ደንበኞች ወርሃዊ ሂሳባቸውን በተጠቀሙት ልክ በወቅቱ እንዲከፍሉ ለማስቻልና የተቋሙን የገቢ አሰባሰብ ሂደትም ቀልጣፋ ለማድረግ በየወሩ የቆጣሪ ንባብ መረጃ በወቅቱና በትክክል መወሰድ ይኖርበታል፡፡ በአሁኑ ወቅት የቆጣሪ ንባብ በትክክል ካለመመዝገብ ጋር በተያያዘ በተቋሙ ገቢ አሰባሰብም ሆነ በደንበኞች አገልግሎት ላይ ችግር ሲፈጠር ይታያል፡፡

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደንበኞቹን ወርሀዊ ሂሳብ ለማስላት በአገር አቀፍ ደረጃ በከፈታቸው 569 የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት ስር የሚገኙ የደንበኞችን የቆጣሪ ንባብ በአንባቢዎቹ አማካኝነት እንዲመዘገብ ያደረጋል፡፡ አስፈላጊው የማጣራት ስራ ከተከናወነ በኋላ የተመዘገበው መረጃ ወደ ሲስተም ይገባል፡፡ ይህ አሰራር ረጅም ጊዜን የሚወስድ፣ አድካሚና  ለስህተት የተጋለጠ በመሆኑ በደንበኞች ዘንድ ቅሬታን ሲፈጠር እንዲሁም በተቋሙ ገቢ አሰባሰብም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሲያሳድር ቆይቷል፡፡

ይህንን ችግር ለመቅረፍ እንዲቻል ተቋሙ በአለም ዓቀፍ ደረጃ ውጤታማነቱ የተመሰከረ የቆጣሪ ንባብ መመዝገቢያ መሳሪያ (Common Meter Reading Instrument) በቅርቡ ወደ ስራ ለማስገባት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

የቆጣሪ ንባብ መመዝገቢያ መሳሪያው ቀድሞ በወረቀት የሚሰሩና ለስህተት የተጋለጡ የንባብ ምዝገባ አሰራሮችን ለማስወገድ የሚያስችልና ዘመናዊና ቀላል ሂደቶችን በመጠቀም ስራን የሚያቀላጥፍ መሳሪያ ነው፡፡

መሳሪያው በአለም ዓቀፍ መሬት አቀማመጥ ስርዓት (Global Positioning System) በመታገዝ የሚሰራ በመሆኑ በየአካባቢው ያሉ የደንበኛ ቆጣሪዎችን መለየት የሚያስችል ነው፡፡ መሳሪያው ሀንድ ሄልድ ዩኒት (Hand Held Unit) የሚባል መተግበሪያ (Application) የተጫነለት በመሆኑ መተግበሪያውን በመክፈት ንባብ የሚወሰድላቸውን ደንበኞች ዝርዝር ለማግኘት ይቻላል፡፡ ማንኛውም የቆጣሪ አንባቢ ሰራተኛ መሳሪያውን በመጠቀም ቆጣሪ ንባብ መመዝገብ የሚችለው ከቆጣሪው ከ50 ሜትርና ከዛ በታች በሆነ ርቀት ውስጥ ሲገኝ ብቻ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን አንባቢው መሳሪያውን በመጠቀም ንባብ መውሰድ አይችልም፡፡

አንባቢው በተወሰነው ርቀቱ ውስጥ ሲገኝ መሳሪያው የደንበኛውን መለያ ቁጥር በመቀበል ንባቡ እንዲመዘገብ ፍቃድ ይሰጣል፡፡ በተጨማሪም የተመዘገበው ንባብ ትክክል መሆኑን አንባቢው እንዲያረጋግጥ ዕድል ይሰጣል፡፡ አንባቢው የሚያስገባው ንባብ ካለፈው ወር ንባብ ያነሰ ከሆነ አይመዘግብም፡፡

የቆጣሪ ንባብ በመሳሪያው ከተመዘገበ በኋላ ተቋሙ በቅርቡ ተግባራዊ ካደረገው የኢ.አር.ፒ ሲስተም ጋር እንዲተዋወቅ በተደረገ የጋራ ሶፍትዌር አማካኝነት ወደ ሲስተም እንዲገባ ይደረጋል፡፡

አንድ አንባቢ የቆጣሪ ንባብ መመዝገቢያ መሳሪያውን መጠቀም የሚችለው የግል የመጠቀሚያ መለያ ስምና የሚስጥር ቁጥር በማስገባት በመሆኑ አንድን የመመዝገቢያ መሳሪያ መጠቀም የሚችለው አንድ አንባቢ ብቻ ነው፡፡ መሳሪያውን ሌሎች አንባቢዎች እንዲጠቀሙበት ሲፈለግ ቀድሞ የነበረው የመጠቀሚያ ስምና የሚስጥር ቁጥር ተሰርዞ በአዲስ መተካት ይኖርበታል፡፡

በዚህ አዲስ የቴክሎጂ ውጤት በሆነ መሳሪያ አማካኝነት የሚካሄድ የቆጣሪ ንባብ ምዝገባ የንባብ ስህተት፣ መረጃ ከአንድ ሰነድ ወደ ሌላው ሲገለበጥ የሚፈጠር የቁጥር ግድፈት፣ የጊዜና የግብዓት ብክነት፣ የደንበኛ ቅሬታ፣ ከተጠያቂነት ጋር ተያያዥ የሆኑ ችግሮችን በመቅረፍ፣ ግልፅና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሰራር እንዲኖር ያግዛል፡፡ የተቋሙንም የገቢ አሰባሰብ አፈጻጸም በዕጅጉ እንደሚያሻሽል ይጠበቃል፡፡

በተጨማሪም መሳሪያው ከተቋሙ ይሁንታ ውጪ የተነካኩ ቆጣሪዎችን ፎቶ በማንሳት ለሚመለከተው የስራ ክፍል መረጃውን ለመላክ የሚያስችል ሲሆን በየወቅቱ የተነበቡና ያልተነበቡ ቆጣሪዎችን በቀላሉ ለመለየት በማስቻል በኩል ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት የመሳሪያው ግዢ የተፈፀመ ሲሆን ለሙያተኞች አስፈላጊ ስልጠና ከተሰጠ በኋላ በቅርቡ ስራ ላይ ይውላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡