በ6 ከተሞች የተገነቡ 11 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኃይል መሙያ ጣቢያዎች ተመረቁ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአገር አቀፍ ደረጃ የአረንጓዴ ኢኮኖሚን ለማሳደግና ሁለንተናዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የሚያስችሉ በስድስት ከተሞች ያስገነባቸውን 11 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኃይል መሙያ ጣቢያዎች በዛሬው ዕለት መርቆ ለአገልግሎት ክፍት አድርጓል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የፌደራል እና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው ተቋሙ ዘመናዊ አሠራሮችንና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አገልግሎቱን ተደራሽ የማድረግ ተልዕኮውን በቁርጠኝነት እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

አዲሶቹ ጣቢያዎች በአዲስ አበባ፣ ቢሾፍቱ፣ ሞጆ፣ ባቱ፣ አዳማ እና ሐዋሳ ከተሞች የተገነቡ ሲሆን፣ በአንድ ጊዜ ለ96 ተሽከርካሪዎች ፈጣን አገልግሎት የመስጠት አቅም አላቸው ብለዋል።

አቶ ጌቱ አክለውም ተቋሙ በአዲስ አበባና በክልሎች ብቻ ሳይወሰን እስከ ጅቡቲ እና ሞያሌ የድንበር ከተሞች ድረስ የቻርጅ ማድረጊያ መስመሮችን ለማስፋፋት በከፍተኛ ትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ አቶ አለማየሁ አሰፋ በበኩላቸው ዛሬ የተመረቁት የቻርጅ ጣቢያዎች የከተማዋን እድገት ለማፋጠን ትልቅ ጥቅም እንዳላቸው ገልፀው የቱሪስት መዳረሻ የሆነችውን ቢሾፍቱ ከተማ የአረንጓዴ ልማት ሥራ ለማረጋገጥ እነዚህ ጣቢያዎች ከፍተኛ አቅም እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

ተቋሙ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ካስገነባቸው 3 ጣቢያዎች ጋር ተደማምሮ፣ በአሁኑ ወቅት 14 ጣቢያዎችን ለአገልግሎት ማብቃት ችሏል።

ይህም በቀን 24 ሰዓት ሙሉ (24/7) እስከ 150 ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚያስችል አቅም ፈጥሯል።

በቀጣይ በሁለት ዙሮች ወደ ሌሎች 14 የክልል ከተሞች ለማስፋፋት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር በመቀሌ፣ በባሕር ዳር፣ በጎንደር፣ በጂጅጋ፣ በድሬዳዋ፣ በጂማ እና በአርባ ምንጭ፤ በሁለተኛው ዙር ደግሞ በጭሮ፣ በደብረ ብርሃን፣ በአምቦ፣ በነቀምቴ፣ በወላይታ ሶዶ፣ በወልቂጤ እና በሆሣዕና ከተሞች ጣቢያዎቹ እንደሚገነቡ ተገልጿል።

በመጨረሻም ተቋሙ በጅቡቲ ኮሪደር ለሚያስገነባው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ (EV) ቻርጅ ጣቢያ ግንባታ የስምምነት ፊርማ ከሁዋዌ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ እና ከቻይና ሮድ ኤንድ ብሪጅ ኮርፖሬሽን (CRBC) ቤጂንግ ፎር ኤቨር ቴክኖሎጂ ጋር በዕለቱ ተከናውኗል።