የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዋነኛ ተልዕኮ ለሕብረተሰቡ የሚያስፈልጉ አገልግሎቶችን በጥራት፣ በተቀላጠፈና በተደራሽ ሁኔታ ማቅረብ ነው። ይህንን ተልዕኮ ለመወጣት ግን አገልግሎት መስጠት ብቻ አይበቃም፤የደንበኞችን ጊዜና ወጪ የሚቆጥብ፣ እንግልትን የሚቀንስና እርካታቸውን ያማከለ አሠራር መዘርጋትም ያስፈልጋል። በዲጂታል ቴክኖሎጂ እየተደገፈ ያለው የዘመናዊ አገልግሎት አቅጣጫም ዜጎች ለአገልግሎት ረጅም ርቀት ከመጓዝና ወረፋ ከመጠበቅ ይልቅ ባሉበት ሆነው እንዲያገኙት ዕድል እየፈጠረ ነው።
በዚህ አቅጣጫ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎ የደንበኞችን ተሞክሮ ለማሻሻል የዘረጋው አዲስ የቴሌግራም ቦት አሠራር ተጠቃሽ ነው። አሠራሩ የቆጣሪ ንባብ ሰራተኞች በተለያዩ ምክንያቶች በተመደበላቸው ጊዜ ንባብ ማከናወን ባልቻሉበት ሁኔታ፣ ተገልጋዮች ወደ አገልግሎት መስጫ ማእከል ሳይሄዱ ንባባቸውን በስልካቸው እንዲያስገቡ ያስችላል። ይህም የጉዞ ወጪንና የጊዜ ብክነትን ከመቀነሱም በላይ በንባብ ሂደት የሚፈጠሩ ክፍተቶችን ለመሙላት የተዘጋጀ ተጨማሪ አማራጭ ነው።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሽያጭና ደንበኞች ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሮ ቤተልሄም ይልማ እንደገለጹት፣ የአዲሱ አሠራር ዋነኛ ዓላማ የደንበኞችን ምቾት ማሳደግና አገልግሎቱን ማቀላጠፍ ነው። “ዋና ዓላማው የደንበኞችን አገልግሎት ምቹ ማድረግ ነው። የቆጣሪ ንባብ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይወሰድ ሲቀር፣ ደንበኞች ካሉበት ቦታ ሆነው ንባባቸውን ማስገባት እንዲችሉ የሚያስችል አሠራር ተዘርግቷል” ብለዋል።
የዚህ አማራጭ ጠቀሜታ በተለይ ከአገልግሎት መስጫ ማዕከላት ርቀው ለሚኖሩ፣በሥራ ምክንያት ወደ አገልግሎት መስጫ ማእከላት ለመሄድ ጊዜ ለማያገኙ ወይም ተጨማሪ የጉዞ ወጪ ለሚያወጡ ደንበኞች የሚታይ ነው። በዚህ መንገድ ደንበኛው የቆጣሪ ንባቡን በተፈቀደው የግዜ ሰሌዳ መሰረት ከቤቱ ሳይወጣ ማስገባት ሲችል፣ተቋሙም የፍጆታ መረጃውን በወቅቱ ለማግኘት ተጨማሪ ዕድል ያገኛል። ይህ በተለይ የቆጣሪ ንባብ ሂደቱ በተለያዩ ሁኔታዎች ሲስተጓጎል የሂሳብ አዘገጃጀቱ በመረጃ እጥረት እንዳይጎዳ ያግዛል፡፡
የቆጣሪ ንባብ በየወሩ የሚከናወን ሲሆን፣ የደንበኛው ወርሃዊ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ሂሳብም በዚሁ መረጃ ላይ ይመሠረታል። ከዚህ ቀደም የቆጣሪ ንባብ ሰራተኞች በተለያዩ ምክንያቶች ንባብ መውሰድ ካልቻሉ፣ ደንበኞች መረጃውን ለማስመዝገብ ወደ አገልግሎት መስጫ ማእከል መሄድ ይጠበቅባቸው ነበር። አዲሱ አሠራር ይህንን ግዴታ በማስቀረት በተፈቀደው የጊዜ ገደብ ውስጥ ንባቡን በቀጥታ እንዲያስገቡ ያስችላል። አገልግሎቱ በተለይ ነጠላ ፌዝ ድህረ ክፍያ ቆጣሪ ለሚጠቀሙ የመኖሪያ ቤት ደንበኞች የተዘጋጀ በመሆኑ፣ ደምበኞች ከመጠቀማቸው በፊት የቆጣሪያቸውን ዓይነትና የንባብ ጊዜ ሰሌዳ ማረጋገጥ አለባቸው።
ኃላፊዋ እንዳብራሩት፣ አዲሱ የቴሌግራም ቦት አሠራር የቆጣሪ አንባቢዎችን ሥራ የሚተካ አይደለም። የቆጣሪ ንባብ ሰራተኞች ወደ ደንበኞች ቤት በመሄድ የቆጣሪ ንባብ ማከናወናቸውን ይቀጥላሉ፤ የቆጣሪ ንባብ በተቀመጠው የግዜ ሰሌዳ ካልተወሰደ ግን ደንበኞች በተከታታይ ባሉት አራት ቀናት ውስጥ በቴሌግራም ቦቱ አማካይነት ንባባቸውን መላክ ይችላሉ። ይህ አሠራር የተለመደውን የቆጣሪ ንባብ ሥራ በማስቀጠል፣ በሂደቱ ውስጥ ሊፈጠር የሚችለውን ክፍተት በዲጂታል አማራጭ የሚሞላ ነው።
የቴሌግራም ቦቱን አገልግሎት ለመጠቀም የተመደበውን የንባብ ጊዜ ማወቅ ወሳኝ ነው። በቃለ መጠይቁ መሠረት፣ በአዲስ አበባ፣ በጅማና በአጋሮ ከተሞች ለሚገኙ ደምበኞች ከወሩ 13ኛ እስከ 26ኛው ቀን ድረስ የደምበኞች ቆጣሪ ንባብ ስራው በተቋሙ ሰራተኞች ይከናወናል፡፡ በዚህ ወቅት የቆጣሪ ንባቡ ካልተወሰደ ከ27ኛ እስከ 30ኛ ቀን በቴሌግራም ቦቱ ትክክለኛውን የቆጣሪ ንባብ ማስገባት ይቻላል።
ለሌሎች ደንበኞችም በቡድን የተለዩ የጊዜ ሰሌዳዎች ተቀምጠዋል። ግሩፕ 1 በወሩ ከ14ኛ እስከ 20ኛው ቀን ቆጣሪ ንባብ የሚወሰድላቸው ሲሆን፣ ካልተወሰደ ከ21ኛ እስከ 24ኛው ቀን በቴሌግራም ቦቱ ንባባቸውን ያስገባሉ። ግሩፕ 2 በወሩ ከ21ኛ እስከ 27ኛው ቀን ንባብ ይወሰድላቸዋል፤ ካልተወሰደ ደምበኞች ከ28ኛ ቀን እስከ ቀጣዩ ወር 1ኛ ቀን ድረስ ደምበኞች የቆጣሪ ንባባቸውን ይችላሉ። ግሩፕ 3 ከ28ኛው ቀን እስከ ቀጣዩ ወር 4ኛ ቀን የቆጣሪ ንባብ የሚወሰድላቸው ሲሆን፣ ካልተወሰደ ከ5ኛ እስከ 8ኛው ቀን በቴሌግራም ቦቱ የቆጣሪ ንባባቸውን መላክ ይችላሉ፡፡ ግሩፕ 4 ድግሞ በወሩ ከ5ኛ እስከ 11ኛ ቀን የቆጣሪ ንባብ የሚወሰድላቸው ሲሆን፣ ካልተወሰደ ከ12ኛ እስከ 15ኛ ቀን ድረስ ደምበኞች መላክ ይችላሉ።
እነዚህ ቀናት በአንባቢዎች ንባብ የሚወሰድበትንና ደንበኞች በራሳቸው ንባብ የሚያስገቡበትን ጊዜ ይለያሉ። በተጨማሪም ደንበኞች ለራሳቸው የተመደበውን ቡድንና የጊዜ ሰሌዳ ከቴሌግራም ቦቱ ማራጋገጥ ይችላሉ፡፡
የቆጣሪ ንባብ መረጃ የወርሃዊ ፍጆታ ሂሳብ መሠረት በመሆኑ፣ በትክክል መመዝገቡ እጅግ አስፈላጊ ነው። የተሳሳተ የቆጣሪ ንባብ በሂሳቡ ላይ ልዩነት ሊፈጥርና ቅሬታ ሊያስከትል ይችላል። ኃላፊዋም ደንበኞች ንባቡን ከማስገባታቸው በፊት በቆጣሪያቸው ላይ የሚታየውን ቁጥር በጥንቃቄ እንዲያረጋግጡ አሳስበዋል። “ደንበኞች ትክክለኛውን ንባብ ማስገባት አለባቸው። ይህ በኋላ ለሚወጣው የፍጆታ ሂሳብ መጠን ጉልህ አስተዋጽኦ አለው። ተቋሙ በአሰራር ስርዓቱ መሰረት የሚላኩ የደንበኞች የቆጣሪ ንባብን የማጣራት ሂደቶችን ቢያከናውንም፣ ደንበኞች የቆጣሪ ንባቡን ከመላካቸው በፊት ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ አለባቸው” ብለዋል።
ደንበኞች በቴሌግራም ቦቱ የሚያስገቡት ንባብ በቆጣሪው ላይ ከሚታየው ቁጥር ጋር መመሳሰሉን ማረጋገጥ አለባቸው። ቁጥሮችን በስህተት መጻፍ፣ አንድን አሃዝ መተው ወይም የቆጣሪውን የተሳሳተ መረጃ መምረጥ የፍጆታ ሂሳቡን ሊያዛባ ይችላል። ስለዚህ ንባቡን ከማስገባት በፊት በጥንቃቄ ማንበብና መረጃ ትክክል መሆኑን ማረጋገጥ የደንበኛው ኃላፊነት ነው። በተቋሙ በኩልም ከሚላኩ የቆጣሪ ንባቦች መካከል ያልተለመዱ ልዩነቶችን የሚለይ የማጣሪያ ሥርዓት መኖሩ የአሠራሩን ታማኝነት ለማጠናከር ይረዳል። ተቋሙም የሚቀርቡትን ንባቦች በተገቢው ሁኔታ የሚያጣራ ሥርዓት ማጠናከርና በመረጃው ላይ ጥያቄ ሲነሳ ደንበኞች የሚያገኙትን የድጋፍ መንገድ ግልጽ ማድረግ ይጠበቅበታል።
አዲስ አሠራር መዘርጋት ብቻውን ውጤታማነቱን አያረጋግጥም። ደንበኞች አገልግሎቱን መቼና እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው በቂ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል። ኃላፊዋ እንደገለጹት፣ ተቋሙ በማኅበራዊ ሚዲያዎች፣ በተቋሙ በአገልግሎት መስጫ ማዕከላት በቆጣሪ አንባቢዎች አማካይነት ስለ አዲሱ አሠራር ግንዛቤ እያስጨበጠ ነው። ቆጣሪ አንባቢዎችም ንባብ ከመውሰድ ባለፈ ለደንበኞች ስለ ቴሌግራም ቦቱ አጠቃቀም ማብራሪያ እየሰጡ ነው።
አገልግሎቱ በተወሰነ የደንበኞች ምድብ ላይ የተጀመረ በመሆኑ፣ የተቋሙ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ የሚመለከታቸውን ደንበኞች በትክክል መድረስ አለበት። የአገልግሎቱ ወሰን፣ የመጠቀሚያ ጊዜና የሚያስፈልጉ መረጃዎች በቀላል ቋንቋ መገለጽ ካልቻሉ፣ ደንበኞች በተሳሳተ ጊዜ ሊጠቀሙበት ወይም አገልግሎቱ ለእነሱ እንደማይመለከት ሳያውቁ ሊቀሩ ይችላሉ። ስለዚህ መረጃውን በተለያዩ የማስተዋወቂያ መንገዶች በተደጋጋሚ ማቅረብ ለአጠቃቀሙ መስፋፋት ጠቃሚ ነው።
አገልግሎቱ ወደ ትግበራ ከገባ አንድ ወር ያህል መሆኑን የገለጹት ኃላፊዋ፣ ከደንበኞች የሚቀርቡ ግብረመልሶች እየተሰበሰቡ መሆኑንም ጠቁመዋል። እነዚህ ግብረመልሶች በትግበራ ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለመለየትና አሠራሩን ለማሻሻል ጠቃሚ ግብዓት ይሆናሉ።
የዲጂታል አገልግሎት ጥቅም በተጠቃሚው በቀላሉ መጠቀም መቻልና ችግር ሲያጋጥመው ፈጣን ድጋፍ ማግኘት ላይም ይመሠረታል። ስለዚህ ተቋሙ የቴሌግራም ቦቱን አጠቃቀም በግልጽ ማስረዳት፣ የሚነሱ ጥያቄዎችን በወቅቱ መመለስና ከትግበራው የሚገኙ ትምህርቶችን በቀጣይ ማሻሻያ ላይ ማዋል ይጠበቅበታል። ይህም የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ከሰው ተኮር አገልግሎት ጋር ተያይዞ መጓዝ እንዳለበት ያሳያል። በዚህ መንገድ የደንበኛና የተቋም ግንኙነት ይበልጥ ቀላልና ቀጥተኛ ይሆናል።
በአጠቃላይ፣ የቴሌግራም ቦት አሠራሩ የቆጣሪ ንባብን ከተቋም አገልግሎት መስጫ ጉዞ ነፃ በማድረግ ለደንበኞች ተጨማሪ ምቾት የሚፈጥር ዲጂታል አማራጭ ነው። የአሠራሩ ዘላቂ ስኬት ግን በቴክኖሎጂው መኖር ብቻ አይወሰንም፤ ትክክለኛ ንባብ፣ ግልጽ የጊዜ ሰሌዳ፣ የደንበኞች ግንዛቤና የተቋሙ ቀጣይ ክትትል ያስፈልጋሉ። ተቋሙ ግብረመልሶችን በመተግበርና የሚነሱ ችግሮችን በመፍታት አሠራሩን ካሻሻለ፣ የደንበኞችን እርካታ ከማሳደጉም በላይ የሕዝብ አገልግሎትን ወደ ተጨማሪ ዲጂታል ለውጥ ለማሸጋገር መሠረት ሊጥል ይችላል።
