የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ ከ95 በመቶ በላይ በመጠን የሚያልፈው በአዲስ አበባ–ጅቡቲ የንግድ ኮሪደር መሆኑ ይህንን መስመር ከመንገድ በላይ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ሕይወት መስመር ያደርገዋል። ከወደብ የሚገቡ የነዳጅ፣ የማሽነሪ፣ የግብዓትና የሸቀጦች ጭነቶች፤ ከሀገር የሚወጡ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችም በዚሁ መስመር ይጓጓዛሉ። የዓለም ባንክ እንደገለጸው፣ ከ95 በመቶ በላይ የኢትዮጵያ የገቢና ወጪ ንግድ በመጠን በኮሪደሩ ይንቀሳቀሳል። ስለዚህ በዚህ መስመር ላይ የሚፈጠር የወጪ፣ የጊዜ ወይም የአገልግሎት መሻሻል በቀጥታ በሸቀጦች ዋጋ፣ በንግድ ተወዳዳሪነትና በሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ አቅም ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።
እስካሁን ድረስ የዚህን ከባድ የጭነት ትራፊክ ዋና ክፍል የሚሸከሙት በነዳጅ/በናፍታ የሚንቀሳቀሱ የጭነት ተሽከርካሪዎች ናቸው። ይህም የነዳጅ ግዥን ብቻ ሳይሆን የውጭ ምንዛሬ ጫናን፣ የትራንስፖርት ወጪን፣ የአየር ብክለትንና ከዓለም ነዳጅ ገበያ የሚመጣ የዋጋ መለዋወጥ ተጋላጭነትን ያበረታታል። የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በ2023 ኢትዮጵያ ለነዳጅ ምርቶች ግዥ ወደ 4 ቢሊዮን ዶላር እንዳወጣች ጠቅሷል። ይህ መጠን የነዳጅ ጥገኝነት ለኢኮኖሚው ያለውን ጫና በግልጽ ያሳያል።
በዚህ የኢኮኖሚ ማነቆ ላይ ምላሽ ለመስጠትና የንጹህ ኃይል አቅሟን ወደ ምርታማ አጠቃቀም ለመቀየር፣ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ትራንስፖርትን እያስፋፋች ትገኛለች። በጥቅምት 21 ቀን 2019 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከሁዋዌ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ፣ ከቻይና ሮድ ኤንድ ብሪጅ ኮርፖሬሽን (CRBC) እና ከቤጂንግ ፎርኤቨር ቴክኖሎጂ ጋር በኢትዮ-ጅቡቲ ኮሪደር ላይ የኤሌክትሪክ መሙያ ጣቢያዎችን ለማልማት የመግባቢያ ስምምነት ፈርሟል።
የስምምነቱ ዋና ትኩረት የግል መኪኖችን ቻርጅ ማድረግ ሳይሆን በየቀኑ በኮሪደሩ ላይ የሚጓጓዙ ከባድ የጭነት መኪኖችን ወደ ኤሌክትሪክ ማሸጋገር ነው። ፕሮጀክቱ፤ የኤሌክትሪክ መኪና አጠቃቀም ከከተማ ውስጥ የግል ተሽከርካሪዎች ተሻግሮ የሀገሪቱን የንግድ አካሄድ ወደሚደግፍ የጭነት ሎጂስቲክስ እንዲደርስ በማድረግ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ። በዚህም የኤሌክትሪክ ኃይል ጥቅም በተሽከርካሪ ባለቤቶች የግል ቁጠባ ብቻ ሳይገደብ በወጪ ንግድ፣ በምርት ሰንሰለትና በአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ገበያ ላይ የሚታይ ተፅዕኖ ይኖረዋል።
ሆኖም ከባድ የጭነት መኪናን በአጭር ጊዜ ኃይል መሙላት ከተለመዱት የመኪና ቻርጀሮች በእጅጉ የበለጠ ኃይል ይፈልጋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው እንዳብራሩት፣ ፕሮጀክቱ በዋናነት በንግድ መስመሩ ላይ የሚመላለሱ ከባድ የጭነት ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ኢላማ ያደረገ ነው። በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ከባድ የጭነት መኪኖች በናፍታ እየተንቀሳቀሱ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የሚሸከሙ በመሆናቸው፣ እነዚህን ወደ ኤሌክትሪክ መቀየር ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ትልቅ እፎይታ ይሰጣል።
ይሁን እንጂ ከባድ የጭነት መኪኖችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ቻርጅ ማድረግ እጅግ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ይጠይቃል። ከባድ የጭነት መኪኖችን በአጭር ጊዜ ለመሙላት እጅግ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ያስፈልጋል። በመሆኑም ለእነዚህ ተሽከርካሪዎች የሚዘጋጁ የፈጣን መሙያ ጣቢያዎች በአንድ ጊዜ ብዙ ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ የሚችል አቅም ሊኖራቸው ይገባል። ስለዚህ አጋር አካላቱ በመጀመሪያ ደረጃ የስድስት ወር ዝርዝር የአዋጭነት እና የግሪድ አቅም ጥናት ያካሂዳሉ። ጥናቱ ጣቢያዎቹ የት አካባቢ ቢገነቡ የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንደሚችሉ፣ የትራፊክ ፍሰቱን እንዴት እንደሚያሳልጡ እና ምን ያህል የኃይል መጠን እንደሚያስፈልጋቸው በትክክል ይለያል። በቅድመ ዲዛይን ደረጃም ከአዲስ አበባ እስከ ጅቡቲ ወደብ ባለው መስመር ላይ በአጠቃላይ 16 ዘመናዊና ፈጣን የኃይል መሙያ ጣቢያዎችን ለመገንባት መታቀዱንም ኢንጂነር ጌቱ አብራርተዋል።
የኢትዮ-ጅቡቲ ኮሪደር እቅድ ከአጠቃላይ ብሔራዊ የኢ-ሞቢሊቲ ፖሊሲ ተነጥሎ የሚታይ አይደለም። በ2024 መጀመሪያ ኢትዮጵያ በቤንዚንና በናፍጣ የሚሠሩ አዳዲስ ተሽከርካሪዎችን ከውጭ ማስገባት ላይ እገዳ በመጣል የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ገበያን ለማበረታታት አቅጣጫ ወስዳለች። በግንቦት 2026 ይፋ የተደረገው የ2025–2030 ብሔራዊ የኢ-ሞቢሊቲ ስትራቴጂም የቻርጅ መሠረተ ልማትን፣ የሕዝብ ትራንስፖርት ሽግግርን፣ የግል ዘርፍ ተሳትፎንና የአካባቢ አቅም ግንባታን የሚያካትት ነው። ስትራቴጂው በ2030 በከተሞችና በክልሎች ከ2,200 በላይ የመሙያ ማዕከላትን ለማስፋፋት እንዲሁም ለከባድ ተሽከርካሪዎች ቢያንስ በ120 ኪሎ ሜትር ርቀት የፈጣን መሙያ አገልግሎት እንዲኖር አቅጣጫ ያስቀምጣል።
ይህን ፖሊሲ በመሬት ላይ ለማሳካት የመሙያ ጣቢያዎች በቂ መሆን ብቻ ሳይሆን የኃይል አቅርቦቱ ተቋማዊ አስተማማኝነት፣ የተሽከርካሪዎች መጠገኛና መለዋወጫ አቅርቦት፣ የባትሪ ደህንነትና የቆሻሻ አያያዝ፣ የክፍያ ሥርዓትና የመረጃ ግንኙነት አብረው መዳበር አለባቸው። ከባድ መኪኖች በተለይ በጭነት መጠን፣ በመንገድ ሁኔታ፣ በከፍታና በአየር ሁኔታ መሠረት የተለያየ የባትሪ ፍላጎት ስለሚኖራቸው፣ የመሙያ ጣቢያዎች ዲዛይን ከእውነተኛው የጭነት እንቅስቃሴ ጋር መጣጣም ይጠይቃል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በጥቅምት 21 ቀን 11 አዳዲስ የመሙያ ጣቢያዎችን በአዲስ አበባ፣ ቢሾፍቱ፣ ሞጆ፣ ባቱ፣ አዳማና ሐዋሳ አስመርቋል። እነዚህ ጣቢያዎች በአንድ ጊዜ 96 ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ ሲችሉ፣ ከቀድሞዎቹ ሦስት ጋር ተዳምረው የተቋሙን ጠቅላላ ጣቢያዎች ቁጥር 14 አድርሰውታል፤ በአንድ ጊዜም እስከ 150 ተሽከርካሪዎችን የመሙላት አቅም አላቸው። ይህ የከተማ መሙያ አውታር ከኮሪደሩ የጭነት ፕሮጀክት ጋር ሲጣመር የሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ትራንስፖርት ሽግግር በተቀናጀ መልኩ እየተስፋፋ መሆኑን ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይሏን በአብዛኛው ከታዳሽ ምንጮች፣ በተለይም ከውኃ ኃይል ታመነጫለች፤ የመንግሥት መረጃ ከሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ምርት 98 በመቶ የሚሆነው ከታዳሽ ምንጮች እንደሚመነጭ ያመለክታል። ይህ ሁኔታ ከነዳጅ ላይ ጥገኛ የሆነውን የመንገድ ጭነት ትራንስፖርት ወደ አገር ውስጥ በሚመነጭ ኃይል ለማንቀሳቀስ ልዩ እድል ይፈጥራል። ከዚህ የሚገኘው ጥቅም የካርቦን ልቀትና የአየር ብክለት መቀነስ ብቻ አይደለም፤ የነዳጅ ወጪን መቀነስ፣ የጭነት ማጓጓዣ ዋጋን ማሳነስና የሀገር ውስጥ ምርቶችን በውጭ ገበያ የበለጠ ተወዳዳሪ ማድረግም ነው።
የኢትዮ-ጅቡቲ ኮሪደርን ወደ ኤሌክትሪክ ጭነት ትራንስፖርት ማሸጋገር በአንድ የቻርጅ ጣቢያ ፕሮጀክት ብቻ የሚጠናቀቅ ጉዳይ አይደለም። የኃይል መረቡን ማጠናከር፣ የጭነት መኪና ገበያን ማበረታታት፣ የግል ዘርፍን ማሳተፍ፣ የቴክኖሎጂ እውቀትን ማስተላለፍና ከጅቡቲ ጋር የሚያስፈልጉ የድንበር ተሻጋሪ የአሠራር ስምምነቶችን ማዳበር ይጠይቃል። እነዚህ ሁኔታዎች በተቀናጀ ሁኔታ ከተፈጸሙ፣ የኢትዮጵያ የንግድ ኮሪደር ከነዳጅ ጥገኝነት ወደ ንጹህ ኃይል በመሸጋገር የሀገር ውስጥ ሀብትን የሚጠቀም፣ የንግድ ወጪን የሚቀንስና የቀጣናዊ ትስስርን የሚያጠናክር ዘመናዊ የሎጂስቲክስ ሥርዓት ሊሆን ይችላል።
በአጠቃላይ:- በኢትዮጅቡቲ ኮሪደር ላይ የሚዘረጋው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የኃይል መሙያ ኔትወርክ የሁለቱን ሀገራት የመሠረተ ልማት ትስስር ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው። ቀደምሲል በኤሌክትሪ ክባቡር መስመር የተጀመረውን የአረንጓዴ ሎጂስቲክስ ትብብር በየብስ ትራንስፖርቱም በመድገም፣ የአፍሪካ ቀንድን የንጹህ ኢነርጂ እና የዘመናዊ ንግድ ቀጣና ለማድረግ የተያዘውን ራዕይ እውን የሚያደርግ ታሪካዊ ፕሮጀክት ሆኖ ይመዘገባል።


