የዓለም አቀፉ የትራንስፖርት ዘርፍ ከአካባቢ ብክለት እና ከነዳጅ ጥገኝነት ለመላቀቅ ወደ ኤሌክትሪክ ተንቀሳቃሽነት (Electric Mobility) የሚያደርገው ሽግግር በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ፍጥነት እየተፋጠነ ይገኛል። በዚህ ዓለም አቀፋዊ የቴክኖሎጂ ሽግግር ውስጥ ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው ታሪክ ግን በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ በምሳሌነት የሚጠቀስ ሆኗል።

ትዮጵያ ታዳሽ ኃይልን በመጠቀም የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል እና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ከቀረጸቻቸው ስትራቴጂዎች መካከል ዋነኛው የትራንስፖርት ዘርፉን ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል (EV) ማሸጋገር ነው። በዚህም መሠረት በ2024 እ.ኤ.አ የነዳጅ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባትን ሙሉ በሙሉ ያገደች የመጀመሪያዋ የዓለም ሀገር ለመሆን በቅታለች።

ይህ ደፋር እና ታሪካዊ ውሳኔ በየዓመቱ ለነዳጅ ግዢ የሚወጣውን ከ6 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ እና ሀገሪቱ ያላትን የተትረፈረፈ ታዳሽ ኃይል በአግባቡ ለመጠቀም ትልቅ ፋይዳ አለው። ለአካባቢ ጥበቃ ከሚኖረው የማይተካ ሚና ባሻገር፣በነዳጅ ግዢ ላይ የሚባክነውን እጅግ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት የተወሰደው ይህ የመንግስት ውሳኔ ፍሬ ማፍራት ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል።   

ይሁን እንጂ ይህ ታላቅ ሀገራዊ ዓላማ ያለ ጠንካራ መሠረተ ልማት ብቻውን ግቡን ሊመታ አይችልም። የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መበራከትን ተከትሎ የኃይል መሙያ ጣቢያዎችን በበቂ ሁኔታ እና በጥራት መገንባት የዚህ ሽግግር ስኬት ወሳኝ ምሰሶ ሆኖ ቀርቧል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደ ሃገራዊ የኃይል አቅራቢ ድርጅትነቱ፤ይህንን የኢቪ ቻርጂንግ መሠረተ-ልማት ልማት እና የኦፕሬሽን ፍኖተ-ካርታ በበላይነት ለመምራት እና ለማስፋፋት ስትራቴጂካዊ ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ተግባር ገብቷል።

በ2026 እ.ኤ.አ መጀመሪያ ላይ በተደረጉ ጥናቶች መሠረት፣በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ115 ሺህ  በላይ (አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ደግሞ ወደ 140 ሺህ የሚጠጉ) የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው በሥራ ላይ ይገኛሉ። ይህ ቁጥር በሀገሪቱ ከተመዘገቡት ጠቅላላ ተሽከርካሪዎች ውስጥ 8.3 በመቶ ያህሉን የሚሸፍን ሲሆን፣ ይህም   ከዓለም አቀፉ ተሽከርካሪዎች አማካኝ ቁጥር 4 በመቶ ነው። ምንም እንኳን ይህ ዕድገት በአሁኑ ወቅት በዋናነት በአዲስ አበባ ከተማ ላይ የተከማቸ ቢሆንም፣ በመንግስት የ10 ዓመት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ (2021-2030) መሠረት እጅግ ሰፊ ስራዎች ይጠበቃሉ። እስከ 2030 ድረስ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ቁጥር ወደ 439 ሺህ ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል።

ከተሽከርካሪዎቹ ቁጥር ፈጣን ዕድገት ጋር የሚመጣጠን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኃይል መሙያ ጣቢያዎች አለመሟላት ለተጠቃሚዎች ዋነኛ ፈተና ሆኖ መቆየቱ አይካድም። ይህንን ግዙፍ ሽግግር ለመደገፍ እና የተጠቃሚዎችን መጉላላት በዘላቂነት ለመቅረፍ በአገር አቀፍ ደረጃ 2 ሺህ 226 የሕዝብ ቻርጂንግ ጣቢያዎችን መገንባት እንደሚያስፈልግ ተለይቷል። ከነዚህም ውስጥ 1 ሺህ 176 የሚሆኑት በአዲስ አበባ ከተማ እንዲሁም ቀሪዎቹ 1 ሺህ 50 ጣቢያዎች ደግሞ በተለያዩ የክልል ከተሞች የሚገነቡ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ይህንን ክፍተት ለመሙላት የሚያስችል ልዩ ትኩረት በመስጠት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በመመደብ ወደ ስራ ገብቷል። ተቋሙ በመጀመሪያው ምዕራፍ በአዲስ አበባ 32 እንዲሁም በሌሎች የክልል ከተሞች 8 በድምሩ 40 የቻርጅ መሙያ ጣቢያዎችን ለመገንባት ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በዚህም መሠረት ባለፈው መጋቢት ወር 2018 ዓ.ም በከፍተኛ ወጪ ተገንብተው ሥራ የጀመሩት የኮተቤ ሳአሊተ ምህረት ፊት ለፊት እና የፒያሳ በቀድሞው የተቋሙ ዋና መስሪያ ቤት ቅጥር ግቢ እና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን (IPDC)  የተገነቡት የኃይል መሙያ ጣቢያዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በቀጣይም ተጨማሪ ጣቢያዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገንብተው አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ።

ተቋሙ በዋና ከተማዋ ብቻ ሳይወስን በሁለተኛው ምዕራፍ በቢሾፍቱ፣ ሞጆ፣ ባቱ፣ አዳማ፣ ሻሸመኔ እና ሐዋሳ ከተሞች ላይ አዳዲስ የኃይል መሙያ ጣቢያዎችን ለመገንባት ዕቅድ ይዟል። ለዚህ ፕሮጀክት ስኬት የሚያስፈልጉ የ34 ፕሮጀክቶች ግብዓቶች፣ ትራንስፎርመሮች እና የተለያዩ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች አስቀድመው ተዘጋጅተዋል።   

በተጨማሪም ከትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በኢትዮ-ጅቡቲ የትራንስፖርት ኮሪደር ላይ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን የመጠቀም ዕቅድ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል። ይህ መሆኑ የትራንስፖርትና የሎጅስቲክስ ወጪን በከፍተኛ ደረጃ ከመቀነሱም በላይ፣ ሀገሪቱ ለነዳጅ ግዢ የምታወጣውን የምንዛሬ ጫና በዘላቂነት ለመታደግ ያስችላል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኢቪ መሙያ መሙያ ጣቢያ መሠረተ-ልማትን በአገር አቀፍ ደረጃ በስፋት፣በጥራት ተደራሽ ለማድረግ የተቀናጀና ዘርፈ-ብዙ አቀራረብ (Hybrid Multi-Model Approach) ስትራቴጂን ይከተላል። ይህ ስትራቴጂ ተቋሙ ከግሉ ዘርፍ ጋር ያለውን አጋርነት የሚያጠናክርባቸውን እና የፋይናንስ ጫናን የሚያቃልሉ አራት ዋና ዋና የንግድ ሞዴሎችን ያካትታል፡-

የመጀመሪያው ሞዴል የቻርጅ ፖይንት ኦፕሬተር ሞዴል (CPO Model) የተሰኘ ሲሆን ይህም   የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ የፋይናንስ እና የኦፕሬሽን ኃላፊነቱን በራሱ በመውሰድ 100 ስልታዊ የቻርጅ መሙያ ጣቢያዎችን በራሱ ተቋማት እና አገልግሎት መስጫ ማዕከላት አካባቢ እንዲገነባ የሚያስችል ነው። ሁለተኛው ደግሞ የጋራ ኢንቨስትመንት ሞዴል (Joint Venture Model) ይባላል፡፡ ይህም ተቋሙ ከግል ባለሀብቶች ጋር በጋራ በመተባበር የካፒታል ወጪንና ስጋትን በእኩል በመጋራት 200 የኤሌክትሪክ ሃይል መሙያ ጣቢያዎችን በከተሞች እና በተለያዩ የንግድ ማዕከላት ውስጥ ለመገንባት ያስችለዋል።

ሶስተኛው አማራጭ "ይገንቡ፣ ያንቀሳቅሱ፣ ያስረክቡ" (BOT Model) የሚባል ሲሆን፣ይህ ሞዴል የግል ባለሃብቶች ሙሉ ወጪውን ችለው ገንብተው ለተወሰነ የኮንሴሽን ስምምነት (a concession agreement) ጊዜ ካንቀሳቀሱ በኋላ መሠረተ-ልማቱን ሙሉ በሙሉ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያስረክቡበት አሰራር ነው። በዚህም በዋናነት በዋና ዋና ብሔራዊ አውራ ጎዳናዎች እና ኮሪደሮች 100 ጣቢያዎችን ለመገንባት ዕቅድ ተይዟል።

አራተኛውና የመጨረሻው የንግድ ሞዴል ተቋሙ በዋና የኃይል አቅራቢነት ሚናው (Energy Supplier Model) በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚገነቡት 2 ሺህ 226 የሕዝብ ኢቪ ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎች እና ከ438 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የመኖሪያ ቤት የኢቪ ቻርጂንግ ጣቢያዎች አስተማማኝ፣ ቀጣይነት ያለውና ንጹህ ኃይል የማቅረብ ሰፊ ኃላፊነት አለበት።

የመሠረተ-ልማት ግንባታው በዘፈቀደ ሳይሆን በሳይንሳዊ ጥናትና ደረጃ በደረጃ የሚከናወን ሲሆን፣ ተቋሙ እስከ 2030 እ.ኤ.አ ድረስ ያለውን የጣቢያዎች ዕድገት፣ የመኖሪያ ቤት መስመሮች ስርጭት እና አጠቃላይ የኃይል ፍላጎትን ያካተተ ግልፅ ፍኖተ-ካርታ አስቀምጧል።

ይህንን ታላቅ ፕሮጀክት እውን ለማድረግ የሚያስፈልጉ መሣሪያዎችን፣የሲቪል ግንባታዎችን እና ትራንስፎርመር ማሻሻያዎችን ጨምሮ ለአንድ ትልቅ የቻርጂንግ ጣቢያ ግንባታ የሚያስፈልገው አጠቃላይ የካፒታል ወጪ ወደ 84.8 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር ይገመታል። ምንም እንኳን የመነሻ ካፒታሉ ከፍተኛ ቢሆንም፣ የፋይናንስ ትንተናው እንደሚያሳየው ፕሮጀክቱ እጅግ አዋጭ እና ኢንቨስትመንቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ መመለስ የሚችል ነው።

የቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎቹ ከፍተኛ አጠቃቀም (High Utilization) ላይ ደርሰው በቀን 360 ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ ቢችሉ፣ የተገቡበትን ኢንቨስትመንት በአንድ ዓመት ከስድስት ወራት ውስጥ ብቻ ሙሉ በሙሉ የሚመልሱ ሲሆን፣ የትርፍ ምጣኔው 68 በመቶ ይደርሳል። በመካከለኛ አጠቃቀም (Medium Utilization) በቀን 240 ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ ቢችሉ  ኢንቨስትመንቱን በሁለት ዓመት ከሁለት ወራት ውስጥ መመለስ የሚቻል ሲሆን የትርፍ ምጣኔው 45 በመቶ ይሆናል። በዝቅተኛ አጠቃቀም (Low Utilization) በቀን 120  ተሽከርካሪዎች ማስተናገድ ቢችሉ እንኳን በአራት ዓመት ከስድስት ወራ ውስጥ ወጪውን ተክቶ 22 በመቶ የትርፍ ምጣኔ ማስመዝገብ ያስችላል።

ከሀገራዊ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አንጻር ሲታይ፣ ይህ ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ መሬት ላይ ሲያርፍ በአገር አቀፍ ደረጃ በዓመቱ ከ422 ሚሊዮን ሊትር በላይ የናፍጣና የነዳጅ ፍጆታን በዘላቂነት ይቀንሳል። ይህም ሀገሪቱ በየዓመቱ ለነዳጅ መግዥ የምታወጣውን ከ422 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ እንድታድን ያደርጋታል። በአካባቢ ጥበቃ ረገድም በዓመት የ1.4 ቢሊዮን ኪሎግራም የካርቦን ዳይኦክሳይድ (CO2) ልቀትን በማስቀረት ረገድ የሚኖረው አስተዋጽዖ ከፍተኛ ነው።    

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚገነባቸው የኤሌክትሪክ ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያ መሠረተ-ልማቶች በዘመናዊ የዲጂታል ቁጥጥር ሥርዓት (Centralized Charging Management System-CMS) የሚመሩ ናቸው። ይህ አሰራር ዓለም አቀፋዊውን የOpen Charge Point Protocol (OCPP) መስፈርት የተከተለ በመሆኑ የሞባይል ክፍያዎችን፣ የQR ባር ኮድ ስርዓትን እና የርቀት መቆጣጠሪያን (Remote Monitoring) ያካተተ ዘመናዊና ቀልጣፋ አገልግሎት ለደንበኞች ለመስጠት ያስችላል። የኃይል ፍላጎቱን ለማመጣጠን እና የኔትወርክ መጨናነቅን ለመቀነስ ስማርት ቻርጂንግ (Smart Charging) እና በጊዜ አጠቃቀም ላይ የተመሰረተ ምክንያታዊ የዋጋ ተመን (Time-of-Use Tariff) ተዘጋጅቷል። በዚህም መሠረት የዋጋ ተመኑ በሶስት የተለያዩ ክፍለ-ጊዜዎች ተከፍሏል፡-

  •   ከምሽቱ 4:00 እስከ ጠዋት 12:00 ሰዓት (Off-Peak Hours)፡- ለአንድ ኪሎ ዋት (kWh) 14.85 ብር፣

  • ከጠዋቱ 4:00 እስከ ቀኑ 11:00 ሰዓት፦ ለአንድ ኪሎ ዋት 16.57 ብር፣

  • ከቀኑ 11:00 እስከ ምሽቱ 4:00 እና ከጠዋቱ 12:00 እስከ 4:00 (Peak Hours)፦ ለአንድ ኪሎ ዋት 18.28 ብር ተደንግጓል።ይህ አሰራር ተጠቃሚዎች የኤሌክትሪክ ሃይል ፍላጎት በሚቀንስበት የሌሊቱ ክፍለ-ጊዜ ቻርጅ በማድረግ የራሳቸውን ወጪ እንዲቆጥቡ ከማስቻሉም በላይ፣ በተቋሙ የኤሌክትሪክ መስመሮች ላይ የሚፈጠርን ከፍተኛ ጫና ይቀንሳል።

በአጠቃላይ የኢቪ ቻርጂንግ ስትራቴጂካዊ ፍኖተ-ካርታ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትን ከተለመደው የኃይል አቅራቢነት እና አከፋፋይነት ሚና ባለፈ፣ ወደ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ሽግግር መሪነት የሚያሻግር ታሪካዊ እርምጃ ነው። አማራጮችን የማስፋትና መሠረተ ልማቶችን የማሟላት ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የነዳጅ አልባ ትራንስፖርት ጉዞ ከዳር ለማድረስ ዋነኛ ዋስትና ነው።

ስትራቴጂው በፋይናንስ ረገድ እጅግ አዋጭ፣ በአካባቢ ጥበቃ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው እና የሃገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ጫና በከፍተኛ ደረጃ የሚቀርፍ በመሆኑ፣ለዘመናዊቷ ኢትዮጵያ የትራንስፖርት ዘርፍ የማይነቅነቅ የጀርባ አጥንት ሆኖ ያገለግላል።